Fana: At a Speed of Life!

ንግድ ባንኮች ከሚያቀርቡት ብድር 5 በመቶውን በተንቀሳቃሽ ንብረት ለሚሰጥ የብድር አይነት እንዲያውሉት የሚያዝ መመሪያ ወጣ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ የሚገኙ ንግድ ባንኮች ከሚያቀርቡት ብድር 5 በመቶውን በተንቀሳቃሽ ንብረት ለሚሰጥ የብድር አይነት እንዲያውሉት የሚያዝ መመሪያ ማውጣቱን ብሄራዊ ባንክ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ተንቀሳቃሽ ንብቶሮችን በዋስትና አስይዞ መበደር የሚያስችለው መመሪያ ላይ ከፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂዷል።

ብሄራዊ ባንኩ ከዚህ በተጨማሪም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች አስይዘው የሚበደሯቸውን ንብረቶች የኢንሹራንስ ተጠቃሚ በሚያደርገው የማይክሮ ኢንሹራን መመሪያ ላይም ከፋይናንስ ተቋማት ተወካዮች ጋር ተወያይቷል።

ከዚህ ቀደም ቋሚ የሆኑ ንብረቶችን ብቻ በማስያዝ ይደረግ የነበረውን የብድር ስርአት ይቀይራል የተባለለት መመሪያው በዋናነት አርሶ አደሩን ፤አርብቶ አደሩን ፤የፈጠራ ባለሙያዎችን እና ሌሎች ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን አስይዘው መበደር የሚችሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ የብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ገልጸዋል።

የብድር ስርአቱ በሀገሪቱ የሚገኙ በተለይም በግብርናው ዘርፍ ያሉ ሀብቶችን አሟጦ ለመጠቀም እንደሚያግዝ የተናገሩት ብሄራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት እና የስራ እድልን በመፍጠርም ጉልህ ድርሻ ያበረክታል ነው ያሉት።

ከዚህ ባለፈም መመሪያው አሁን ላይ በሀገሪቱ በሁሉም ዘርፎች ያለውን የተበዳሪዎች ቁጥር ከ260 ሺህ በላይ እንደሚያሳድግ እና ለፋይናንስ ዘርፉ አዲስ መንገድን ከፋች መመሪያ መሆኑን ዶክተር ይናገር ደሴ ተናግረዋል።

ዶክተር ይናገር ደሴ መመሪያ ባንኮች በዓመት ለተለያዩ ዘርፎች ለብድር ከሚያቀርቡት ገንዘብ ውስጥ 5 ከመቶ የሚሆነውን ለተንቀሳቃሽ ንብረት ለሚያቀርቡ ተበዳሪዎች ማዘጋጀት እንዳለባቸው መመሪያው እንደሚያዝ ገልጸዋል።

የብሄራዊ ባንክ በቀጣይ ዓመት መመሪያው ተግባራዊ እንዲደረግ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑን የገለጹት ገዥው ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን አስይዘው መበደር የሚፈልጉ ዜጎችን ለመመዝገብ በማእከል ደረጃ የመመዝገቢያ ስርዓት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ተንቀሳቃሽ ንብረቶችን አስይዞ መበደርን የሚፈቅደው አዋጅ በተወካዮች ምክር ቤት በዘንድሮ ዓመት መጽደቁ ይታወሳል።

በጥበበስላሴ ጀምበሩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.