Fana: At a Speed of Life!

ኖርዌይ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋገጠች

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኖርዌይ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት በሁለንተናዊ መልኩ አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ የኖርዌይ አምባሳደር ሜሬት ሉንደሞ አስታወቁ።

አምባሳደሯ ይህንን ያስታወቁት በዛሬው ዕለት ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጋር በዘርፈ-ብዙ የትብብር እና በወቅታዊ ጉዳዮች በተወያዩበት ወቅት ነው።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በውይይቱ ወቅት፥ ኢትዮጵያ የሁለቱን ሀገራት ግንኝነት እና ብሔራዊ ፍላጎት ለማስጠበቅ በሚያስችል መልኩ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ በሁሉም ዘርፎች መጠናከሩን እንደምትፈልገው ገልጸዋል።

ኖርዌይ በተለይ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ የዕውቀት እና የክህሎት ሽግግር በማድረግ ላበረከተችው ሚና ምስጋና አቅርበዋል።

ዶክተር ነገሪ ሌንጮ በአሁኑ ስዓት የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል ያካሄደው የሕግ ማስከበር ዘመቻ በወሳኝ መልኩ መጠናቀቁን ጠቁመው፤ በጽንፈኛው የሕወሓት ኃይል ጉዳት የደረሰባቸውን መሠረተ ልማቶች መልሶ የመገንባት እና የአካባቢውን ማሕበረሰብ ሰላም የማረጋገጥ ሥራ ቅድሚያ ተሰጥቶት እየተሠራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

አይይዘውም መንግስት ችግሩን ለመፍታት ከትግራይ ተወላጆች የተውጣጣ ግዜያዊ አስተዳደር አቋቁሞ ወደ ትግበራ መግባቱን እንዲሁም ከሕግ ማስከበር ዘመቻው ጎን ለጎን የሰብዓዊ ርዳታ ድጋፎችን አጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።

አምባሳደር ሜሬት ሉንደሞ በበኩላቸው፥ የሀገራቱ ሁለትዮሽ ይፋዊ ግንኙነት በይፋ ከተጀመረ ሩብ ምዕተ ዓመት የዘለለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግኑኝነታቸውም በብዙ መስኮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል።

ትብብሩ በዋናነት የትምህርቱን ዘርፍ የጥራት ደረጃ በማሻሻል፣ የባለሙያዎችን ዓቅም በመገንባት፣ የአረንጓዴ አኮኖሚን ግንባታ ጥረት በመደገፍ፣ የደን እና የደን ተዋፅዖችን በአግባቡ የመጠቀም ባሕልን ከማዳበር አኳያ እንዲሁም የዜጎችን ሰላም እና ደህንነት ከማረጋገጥ አንጻር በቅርበት እንደሚሠሩም አምባሳደሯ አብራርተዋል።

አምባሳደር ሉንደሞ አክለውም ኖርዌይ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ሥር-ነቀል ለውጥ አጥብቃ እንደምትደግፍና  በተለይም በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ፣ በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ እና በመሰል ጉዳዮች በቅርበት መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ አስረድተዋል።

አያይዘውም የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል ያካሄደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ በአጭር ጊዜ ማጠናቀቁን ተከትሎ በክልሉ ለሚገኙ ተጎጂዎች ሰብዓዊ ርዳታ ለማድረስ እና ክልሉን መልሶ ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ጥረት መንግስታቸው በሙሉ ዓቅም እንደሚደግፉት ገልጸዋል።

ከዚያም ባለፈ መንግስት ከዓለም-አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች እና ምግባረ-ሰናይ ተቋማት ጋር ትብብሩን አጠናክሮ በመቀጠል ዜጎችን በአጭር ግዜ ውስጥ ወደ ሰላማዊ እንቅስቀሴ ለመመለስ የሚያደርገውን ጥረት በበጎ እንደሚያዩት መናገራቸውን ከህዝብ ተወካች ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.