Fana: At a Speed of Life!

ኖቭል ኮሮና ቫይረስ ልየታ ስራ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮላፕላን ማረፊያ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኖቭል ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ሁሉም መንገደኞች የሰውነት ሙቀት ልየታ ስራ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መጀመሩ ተገለፀ።

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ በሽታን አስመልክቶ በዛሬው እለት መግለጫ ሰጥቷል።

በመግለጫው የዓለም ጤና ድርጅት የኖቭል ኮሮና ቫይረስ በሽታ ከታሕሳስ 21 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በቻይና ዉሃን ክልል መከሰቱን አስታውቋል።

ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ መከላከል ዝግጅት መደረጉንም ነው ኢንስቲቲዩቱ በመግለጫው ያስታወቀው።

ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር የአየርና የየብስ ትራንሰፖርት ትስስር የምታደርግ ሲሆን፥ በሽታውን ሪፖርት ካደረጉ ሃገራት ጋርም በአየር መንገዷ አማካኝነት በርካታ በረራዎች አሏት ብሏል ኢንስቲትዩቱ በመግለጫው።

በመሆኑም በማንኛውም የአየር መንገድ በኩል ለሚሄዱ መንገደኞች ለቫይረሱ ተጋላጭ እንዳይሆኑ ስለ በሽታው መረጃ መስጠት እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡት ደግሞ በበሽታው ተይዘው ሊሆን ስለሚችል በዓለም የጤና ድርጅት ምክረ ሀሳብ መሰረት ለሁሉም መንገደኞች የሰውነት ሙቀት ልየታ ስራ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መጀመሩን ገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት የተለያዩ የዝግጁነት ስራዎችን የጀመረ ሲሆን፥ ለክልሎች እና ለባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን የዝግጅት ስራዎች እንዲያከናውኑ የቅድመ ዝግጅት መልዕክት አሰራጭቷል።

በቻይና እንደተከሰተ በተገለፀው ቫይረስ እስከ ዛሬ ጥር 15 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በጠቅላላ በተለያዩ ሀገራት 581 ታማሚዎች ሪፖርት ተደርጓል።

571 የሚሆኑት ታማሚዎች ከቻይና ብቻ ሪፖርት የተደረጉ ሲሆን፥ ከእነዚህ ታማሚዎች ውስጥ 26 የሚሆነት ህይወታቸው ማለፉን መረጃዎች ያመላክታሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.