Fana: At a Speed of Life!

አለም አቀፉን የፅዳት ቀን በንቅናቄ ለማሳለፍ ዝግጅት ተደርጓል- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ)አለም አቀፉን የፅዳት ቀን በንቅናቄ ለማሳለፍ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አወቀ ሀይለማርያም እና የደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር እሸቱ ለማ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በነገው እለት የሚከበረውን የአለም አቀፍ የፅዳት ቀን በፅዳት ንቅናቄ ለማሳለፍ ዝግጅት መደረጉን ገልፀዋል።

ባለፉት ጊዜያት ከፅዳት ጋር በተያያዘ ሰፊ ስራ መሰራቱን ያነሱት ሃላፊዎቹ ስራውን በዘመቻ ብቻ ከመስራት ይልቅ የየእለት ተግባር ለማደረግ ይሰራል ብለዋል።

በነገው እለትም ከማለዳው 12 ሰአት ጀምሮ በመንግስት ተቋማት፣ በትምህርት ቤቶች ፣በሀይማኖት ተቋማት የፅዳት መርሃግብር ይካሄዳል ብለዋል።

በዚህም መላው የከተማዋ ነዋሪ በንቅናቄው እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ለፅዳት መርሃግብሩ አካባቢዎች መለየታቸውን ያነሱት ሃላፊዎቹ፤በነገው እለትም ፅዳትን በመጠበቅ የተሻለ አፈፃፅም ያላቸው አካባቢዎች እውቅና እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል።

አዲስ አበባ እንደአለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ መቀመጫነቷ እና የሀገሪቱ መዲናነቷ ፅዱ፣ ውብ እና አረንጓዴ ማድረግ የሁሉም ሃላፊነት ያሉ ሲሆን በአረንጓዴ አሻራው የታዬው ንቅናቄም በፅዳት ሊደገም ይገባል ብለዋል።

በሀብታሙ ተክለስላሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.