Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ በኮቪድ-19 በፅኑ ለታመሙ የሚሆኑ 250 ሜካኒካል ቪንቲሌተሮችን ለኢትዮጵያ ሰጠች

አዲስ አበባ ፣ሐምሌ 28 ፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አሜሪካ ኢትዮጵያ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ 250 ሜካኒካል ቪንቲሌተሮች ድጋፍ አደረገች።

ድጋፉን ያስረከቡት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምሳደር ማይክል ራይነር ሲሆኑ፥ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ተረክበዋል።

ሜካኒካል ቬንቲሌተር በኮቪድ-19 በጽኑ ለታመሙ የአየር ሥርዓት ፍሰትን ለማስተካከል የሚረዳ መሳሪያ ሲሆን÷ የቫይረሱ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ በዓለም ላይ እጅግ ተፈላጊና ውድ መሳሪያ መሆኑ ተጠቅሷል።

ዛሬ ድጋፍ የተደረገው የሜካኒካል ቬንቲለተር የአንዱ ዋጋ 8 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ሲሆን÷ አጠቃላይ ዋጋ 70 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ነው።

በኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ ድርጅት ቅጥር ግቢ በተካሄደ የርክክብ ስነስርዓት ላይ አምባሳደር ማይክል ራይነር÷ ኮቪድ-19 የዓለም ቀውስ ሆኖ በቀጠለበት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ዜጎቿን ከዚህ በሽታ ለመጠበቅ ሰፊ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኗን ጠቁመው÷ ይህንን ጥረት ለመደገፍም የአሜሪካ መንግስት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ዛሬ 250 መሣሪያዎች ድጋፍ ማድረጉን በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ነው የገለፁት። ወደፊትም  ሀገራቸው ኢትዮጵያ የምታደርገውን ጥረት ለማገዝ ድጋፉ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በቀጣይም 250 ሜካኒካል ቪንቲሌተሮችን ለማምጣት በሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው÷ ኮቪድ -19 ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን በመግለፅ  በዚህም ቅዳሜ ዕለት ሀገር አቀፍ የምርመራ መርሃ ግብር ይፋ መደረጉን አስታውሰዋል።

የአሜሪካ መንግስት በዚህ የወረርሽኙ መከላከል ስራ ላይ ሀገሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያጥራትን የሜካኒካል ቬንቲሌተር ማበርከቱ ትልቅ ትርጉም አለው ነው ያሉት።

ይህም ድጋፍ ኢትዮጵያ ያላትን የሜካኒካል ቬንቲሌተር ቁጥር በእጥፍ ያሳደገ መሆኑን ተናግረው÷ በቀጣይም እንደዚህ አይነት ድጋፎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የመተንፈሻ መሳሪያዎቹን የኢትዮጵያ መድሀኒት አቅራቢ ድርጅት ወደ ክልሎች የሚያሰራጭ መሆኑም ነው የተገለጸው።

በፍሬህይወት ሰፊው

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.