Fana: At a Speed of Life!

አሜሪካ ከሆንግ ኮንግ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ለቻይና ባለስልጣናት ቪዛ ከለከለች

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 20 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አሜሪካ ከሆንግ ኮንግ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በቻይና ባለስልጣናት ላይ የቪዛ ክልከላ መጣሏን አስታወቀች፡፡

የቪዛ ክልከላው የአሁን እና የቀድሞ የሃገሪቱን ባለስልጣናት እንደሚያካትት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ ተናግረዋል፡፡

ክልከላው ቤጂንግ የሆንግ ኮንግን ሉዓላዊነት ጥሳለች በሚል ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው በተባሉ ባለስልጣኖቿ ላይ የተላለፈ ውሳኔ ነው ተብሏል፡፡

ውሳኔው የአሜሪካ ሴኔት ቻይና በሆንግ ኮንግ ትፈጽመዋለች ላለው የህግ ጥሰት የሃገሪቱ ባለስልጣናት እና ከባለስልጣናቱ ጋር አብረው ይሰራሉ ባላቸው ባንኮች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ያሳለፈው የውሳኔ አካል መሆኑም ተነግሯል፡፡

ይሁን እንጅ የቪዛ ክልከላው የሚመለከታቸው የቻይና ባለስልጣናት ማንነት አልተገለጸም፡፡

በዋሽንግተን የቻይና ኤምባሲ ውሳኔውን ስህተት ነው በሚል ኮንኖታል፡፡

ኤምባሲው በመግለጫው አሜሪካ ስህተቷን በማረም ውሳኔዋን እንድትተውና በቻይና የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባቷን ማቆም እንዳለባት አሳስቧል፡፡

ቻይና ከሰሞኑ በሆንግ ኮንግ ላይ ያላትን የስልጣን ገደብ በሚመለከት የፀጥታና ደህንነት ህግ አርቅቃለች፡፡

አዲሱ ህግ ቤጂንግ በሆንግ ኮንግ ላይ አለኝ ከምትለው የባለቤትነት መብት በተቃራኒው የቆሙ አካላትን በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑም ነው የተነገረው፡፡

ምንጭ፡-ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.