Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ከተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 4፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኩባ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ከተለያዩ ሃገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ሽብሩ ተቀማጭነታቸውን በሀቫና ካደረጉ የወቅቱ የተመድ ተለዋጭ አባል ሀገር ከሆነችው ከህንድ ማዱ ሴቲ፣ ከባህማስ አንድሪው ብሬንት፣ ከሁዱራንስ አንድሬስ ፓቮነ ሙሪሎ እንዲሁም ከሃይቲ ሬጂን ላሙር ጋር በቀጠናዊና የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ አምባሳደር ሽብሩ ኢትዮጵያ የአባይ ውሃን 86 በመቶ አመንጭና ከ60 በመቶ በላይ ዜጎቿ መብራት አልባ የሆኑባት ሃገር ከድህነት ለመውጣት እየሰራች ያለው ፕሮጀክት እንጂ የታችኞቹን ተፋሰስ ሃገራት ለመጉዳት እንዳልሆነ፣ የአባይን ውሃ ፍትሐዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ የዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ህግን ባከበረ መልኩ እየገነባች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የውሃ ሙሌቱ የግንባታው አካል እንደሆነ፣ የሶስትዮሽ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በኢትዮጵያ በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ለአምባሳደሮች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በኢትዮ-ሱዳን የድንበር ውዝግብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ያላትን ጽኑ እምነት እንዲሁም በትግራይ ክልል ስላለው ሰብአዊ ድጋን በተመለከተ በመጀመሪያ ዙር ለ4 ነጥብ5 ሚሊየን ዜጎች ድጋፍ መደረጉንና ሁለተኛ ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ መጀመሩንም አብራርተዋል፡፡

እንዲሁም ለሰብዕዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና የዓለምአቀፍ ሚዲያ ተቋማት ያልተገደበ ፈቃድ መስጠቱን ጨምሮ ሌሎች ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተገናኝ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጋር የጋራ ምርመራ ለማድረግ እየተከናወኑ ስላሉ ስራዎችም ገለጻ አድርገዋል።

በተጨማሪም ስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅና የሰጣቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የነቃ ተሳትፎ የሚያደርጉበት ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ እና የዓለም አቀፍ ማህበረሰቡም በታዛቢነት መጋበዙን ለአምባሳደሮቹ ገልጸውላቸዋል።

ከአምባሳደሮቹ ጋር በሁለትዮሽ እና በቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ የሀሳብ ልውውጥ ማድረጋቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.