Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ የመንግስትን የህግ የማስከበር ዘመቻ ለሱዳን መንግስት ገለጻ አደረጉ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 14፣ 2013 (ኤፍቢሲ) በሱዳን የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር አቶ ይበልጣል አዕምሮ ለሱዳን የመከላከያ ሚኒስትር ሌፍተናንት ጄኔራል ያሲን ኢብራሂም ያሲን አብደልሃዲ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ገለጻ አድርገዋል፡፡

አምባሳደሩ በገለጻቸው የሁለቱን ሀገራት የጋራ ድንበር ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ እንዲሁም በስደተኞች አያያዝ ዙሪያ በሱዳን መንግስት እየተደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

በመቀጠልም የትህነግ የጥፋት ቡድን ለ27 ዓመታት ስለፈፀመው ዝርፊያና ወንጀል በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ስለፈፀመው አስነዋሪ ጥቃት እና ተያያዥ ጉዳዮችን አብራርተውላቸዋል፡፡

አምባሳደሩ በማያያዝም የህወኃት ቡድንን ወደ ፍትህ ለማምጣት መንግስት ስለወሰደው ህግ የማስከበር እርምጃ እና ሂደቱ ስለደረሰበት ደረጃ በዝርዝር ማንሳታቸውን በሱዳን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ገልጿል፡፡

ሚኒሰትሩ በበኩላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሱዳን የሰላም ሂደት ያበረከቱትን አስተዋፅዖ አስታውሰው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር እንደ ጎረቤት ሀገር የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅርበት እንደሚከታተሉ ጠቅሰው የኢትዮጵያ የሰላም ሁኔታ እንደሚያሳስባቸውና እንደ ኤርፖርት ያሉ የመሰረተ ልማት አውታሮችን ማፈራረስና ንፁሃን ዜጎችን መግደል ተቀባይነት የሌለው ተግባር መሆኑን ነው ያነሱት፡፡

በመጨረሻም ህግ የማስከበሩ ሂደት ከደረሰበት ደረጃ አንፃር ችግሩ ባጠረ ጊዜ እልባት ያገኛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው እንዲሁም የጋራ ድንበሩን ፀጥታና ደህንነት ለማስከበር ከኢትዮጵያ ጋር ይበልጥ ተቀራርበው የሚሰሩ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.