Fana: At a Speed of Life!

አምባሳደር ዮናስ ዮሴፍ በታንዛኒያ  ለሚገኙ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሚዲያዎች ገለጻ አደረጉ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዝያ 11 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በታንዛንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር  ዮናስ ዮሴፍ ለታንዛኒያ  የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች እንዲሁም  ለአለም አቀፍ ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሰጡ።

በዚህም በትግራይ ክልል የህውሓት ቡድን በአገር መከላከያ ራዊት የሰሜን እዝ ላይ የወሰደውን አሰቃቂ እና ያልተጠበቅ ጥቃት ተከትሎ የፌደራሉ መንግስት የወሰደውን ህግን የማስከበር ስራ ከመነሻው ጀምሮ አሁን እስካለበት ምእራፍ ያለውን ሁኔታ አስገንዝበዋል።

በአሁኑ ወቅት የመልሶ ግንባታ እና የሰብአዊ ድጋፍ የማድረሱ ስራ ተጠናክሮ በመሰራት ላይ ነው ያሉት አምባሳደሩ የኢትዮጵያ መንግስት በሙሉ አቅሙ ክልሉን መልሶ ለመገንባት እና በጦርነቱ የተጎዱ ዜጎችን የመርዳት ስራ እያከናወነ እንዳለ አስረድተዋል።

ከዚህ በተጫማሪም የሰብአዊ ጥሰቶችን በተመለከተ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ስራ ከአፍሪካ ህበረት እና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ድርጅት ጋር በመተባባር በመመርመር አጥፊዎችን ልህግ የማቅረቡ ስራ እንደሚሰራ አረጋገጠዋል።

የህዳሴውን ግድብ በተመለከተም የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት በተጀመረው መልኩ እንዲቋጭ አቋሙ መሆኑን እና ይህም እንዲሳካ በድርድሩ ላይ በቀና ልቦና በመሳተፍ ላይ ናት ብለዋል።

በተመሳሳይ መልኩ ሁለቱ የታችኛው ተፋሰስ አገራትም በቀና ልቦና የሚሳተፉ ቢሆን ኖሮ ከስምምነት ለመድረስ ይቻል ነበር ብለዋል።

ሁለቱ አገራት በአፍሪካ ህብረት የተጀመረውን ድርድር ወደጎን በመተው ጉዳዩ አለም አቀፋዊ ለማድረግ በተለይም የአረብ የሴኩሪቲ አጀንዳ አድረገው ለማቅረብ መጣራቸውን ኮንነዋል።

ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ጉዳይ በተመለከተም ኢትዮጵያ ጉዳዩ ሰላማዊ በሆነ መልኩ በድርድር እንዲፈታ ከፍተኛ ፍላጎት ያለት መሆኑን ጠቁመው ÷ ይህንን ለማመቻቸትም የሱዳን ሰራዊት በህገወጥ መልኩ በጉልበት የያዘውን መሬት በመልቀቅ ቀድሞ ወደ ነበረበት ቦታ እንዲመለስ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የሱዳንን ተግባር በመኮነን አስፈላጊውን ጫና ሊያሳድር ይገባዋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት ፈጽሞ የላትም ያሉት አምባሳደሩ ÷ሱዳን የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ሆና ሳለች የአባል አገርን ድንበር በመጣስ በቀጠናው አለመረጋጋት እንዲፈጠር ምክንያት እየሆነች ነው ብለዋል።

የምርጫ ጉዳይን በተመለከተም 6ኛው አገራዊ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ እና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት ያደረገ መሆኑን፣ አለም አቀፍ ታዛቢዎች የምርጫ ሂደቱን እንዲታዘቡም ሁኔታዎች የተመቻቹ መሆኑን በመግለጽ እንደ አስፈላጊነቱ በቀጣይ የሚኖሩ ክስተቶችን ለሚዲያው የሚገለጽ መሆኑን ማብራራታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጥህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.