Fana: At a Speed of Life!

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው መግለጫ የተዛባና ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑን የአማራ ክልል ገለፀ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 23፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው መግለጫ የተዛባና ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑን የአማራ ክልል ገለፀ።

የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙልነህ ጉዳዩን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫውም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በአማራ ክልል በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር ዞኖች በነበረው ችግር ላይ ያቀረበው ሪፖርት ከግጭቱ መነሻ ምክንያት ጀምሮ በርካታ ክፍተቶች ያሉት፣ የተዛባና በአንድ ወገን መረጃዎች ላይ የተመሠረተ ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑን ነው ዳይሬክተሩ የገለፁት።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ግጭት ተፈፀመባቸው በተባሉ ቦታዎች የአማራ ተፈናቃዮች፣ መሠረታዊ የሆኑ የክልሉ መንግስት አመራሮች እና ተቋመት ተጠይቀው ተገቢ መረጃ ተሰብስቦ ሳይካተት ሚዛናዊነት በጎደለው ሁኔታ መግለጫ መስጠቱ መታረም እንዳለበት ተናግረዋል።

ሪፖርቱ በቅማንት ላይ የብሄር ጥቃት እንደተፈፀመ እና ቅማንት ብቻ የጠፈናቀለ አድርጎ ማቅረቡ ሁለቱን ህዝቦች እንደገና ወደቁርሾ የሚመራ፣ ለአንድ ወገን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንደተፈፀመ የሚገልፅ ትክክለኛነት የጎደለው ነው ብለዋል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል የክልሉ መንግስት እና የፌደራል መንግት የሠሩትን ስራ እውቅና በመንፈግ አንድ ወገንን ማዕከል አድርጎ ሪፖርቱን ማዘጋጀቱ ለሪፖርቱ ሚዛናዊ አለመሆን ማሳይ አድርገው አቅርበዋል አቶ ግዛቸው።

በመሆኑም ድርጅቱ ያወጣውን መግለጫ እንደገና እንዲመለከተው ጠይቋል።

በናትናኤል ጥጋቡ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.