Fana: At a Speed of Life!

አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው መግለጫ የተሳሳተና ሚዛናዊነት የጎደለው ነው- የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 22፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው መግለጫ የተሳሳተ እና ሚዛናዊነት የጎደለው መሆኑን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ገለፀ።

የክልሉ መንግስት አምነስቲ ኢንተርናሽናል የመንግስት የፀጥታ አካላት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሰብዓዊ መበት ጥሰት ፈፅመዋል ሲል  ባወጣው ሪፖርት ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ሪፖርቱ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ እና ሊታረም የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል።

አምነስቲ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን እየተከታተለ ይፋ የሚያደርግ ሆኖ ሳለ የመንግስትን ምላሽ ባላካተተ መልኩ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት ብቻ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን አስተያየት በመቀበል ያወጣው መረጃ መሆን የማይግባው ነበር ብለዋል።

ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ሲፈፀሙ በነበሩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ዝምታን የመረጠ፣ በተለይም ነፍጥ ያነገቡ ታጣቂዎች በተለያዩ አካባቢዎች በሕዝብና የመንግሥት ኃይሎች ላይ የሚፈፅሙትን ወንጀል የካደ እና የተጎጂዎችን ድምፅ ያላሰማ ይልቁንስ የአንድን ወገን ፍላጎት ለማጉላት ጥረት ያደረገ በመሆኑ ተቀባይነት የሌለው ነው ብለዋል።

ድርጅቱ ያወጣውን ሪፖርት ሚዛናዊነቱን በጠበቀ መልኩ ዳግም ማስተካከል የሚፈልግ ከሆነ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

ሃላፊው በሌሎች የክልሉ ወቅታዊ ሁኔታ ላይም አያይዘው መግለጫ ሰጥተዋል።

በዚሁ መግለጫም አሁን ላይ በክልሉ በተለያየ መልኩ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሀገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ ባላገናዘበ መልኩ የሚጠሩት ሰላማዊ ሰልፍ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስታውቀዋል።

 

በትዝታ ደሳለኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.