Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው የትህነግ ቡድን አለኝ ከሚለው የደጀን ኃይሉ እየራቀ በመጣ ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ወጥመዱ እየገባ በመሆኑ ወደ መቃብር መውረዱ የማይቀር ነው – የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ

 

አዲስ አበባ ፣ ሐምሌ 29 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የትህነግ ቡድን የደጀን ኃይሉ እየራቀ በመጣ ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደ ወጥመዱ እየገባ በመሆኑ ወደ መቃብር መውረዱ የማይቀር እንደሆነ የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ አስታወቀ።

ድል ያለመስዋዕትነት የማይታሰብ ነው ያለው መግለጫው፣ በግንባር የሚገኘው የወገን ጦር ፊት ለፊት ጠላትን እየሰበረ እንደሚገኝ የገለጸው የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ፤ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ወደወጥመዱ እየተሳበ ወደመቃብር ማውረዱን ይቀጥላል፤ የምስራቅ አማራ ሰሜን ወሎ ተራሮች የወራሪው ትህነግ መንጋ መቀበሪያ ይሆናሉ ብሏል።

ታሪካዊ ከተሞቻችንም ሆነ አጠቃላይ የአማራን ግዛት ከጠላት ወረራ መመከት የሚቻለው በጠንካራ አደረጃጀት፣ በወታደራዊ ዲሲፕሊን እና በትግል ዓላማ ጽናት በመታገል እንደሆነ አስረድቷል፡፡

ጠላት በየአቅጣጫው የሚነዛቸው የሽብርና ፈጠራ ወሬዎች በትግላችን ላይ ተጽዕኖ እንዲኖራቸው መፍቀድ እንደማይገባ ያመለከተው መግለጫው፤ ጠላት አለኝ ከሚለው የደጀን ኃይሉ እየራቀ በመጣ ቁጥር ከመቼውም ጊዜ በላይ ወደወጥመዱ እየገባ መሆኑንና ያለምህረት የምንቀጣው በዚህ አግባብ እንደሆነም ጠቁሟል፡፡

ምንጫቸው ባልታወቁ የጠላት ወሬዎች ከመደናገር ራሳችን መቆጠብ እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
ምንግዜም ቢሆን የመረጃ ምንጮቻችን በሙሉ የኃላፊነት ስሜት የሚንቀሳቀሱት የሕዝባችን ሚዲያዎች እና በየደረጃው ያለው አመራር እንጅ የጠላት ኃይል ሊሆን እንደማይገባም አመልክቷል፡፡

የአርሶ አደሩን ጎተራ ሊያራቁት፣ ሚስቱን ሊደፍር፣ ልጁን ሊያፍን፣ ወጣቶቹን ሊገድል፣… የመጣውን መንጋ ህዝቡ በቆራጥነት ስሜት እየተፋለመው እንደሆነም አመልክቷል፡፡

መግለጫው አክሎም በየጫካውና ሰርጡ እየተሳደደ ያለው አሸባሪ ሃይል ከአማራ መሬት በድን ሬሳው እንጂ ከእነ እስትንፋሱ እንዲወጣ አንፈቅድለትም፡፡ ከውጊያ ግንባሮች ርቀው የሚገኙ የአማራ ልጆች፣ የክልሉ ሕዝብና መላ ኢትዮጵያውያን በጠላት ትህነግ የሚነዛውን ሐሰተኛ ወሬ ቦታ ባለመስጠት የሥነ-ልቦና ጦርነቱን በበላይነት መምራት ይኖርብናል ሲልም አስገንዝቧል ፡፡

“ጠላት ጨርሶ ወደ መቃብር መውረዱ አይቀሬ ስለመሆኑ በእርግጠኝነት የምንናገረው ነው፡፡ የሰው ልጅ ቀርቶ እንስሳት እንኳ በጦርነት ሕይወታቸው እንዲያልፍ የማንሻ ቢሆንም፣ ወራሪን መቅጣት ጥንትም የአባቶቻችን ነውና ሞት ምርጫው ለሆነ ጠላት ምህረት የለንም፡፡ በማዕበል የሚዝል ክንድ እንደሌለን የሰሜን ወሎ ተራሮች ዘላለማዊ የታሪክ ምስክር እናደርጋቸዋለን” ሲል መግለጫው አመልክቷል።

በአንፃሩ ከደጀኑ የሚርቅ ጠላት ለሞት የተሰለፈ በመሆኑ ወደ መቃብር መውረዱ እንደማይቀር የጠቆመው የአማራ ክልል ብልፅግና ፓርቲ፣ ትርጉም በሚሰጥ መስዋዕትነታችን ታሪካዊ ከተሞቻችንን ብቻ ሳይሆን የአማራን ሕዝብ እና የኢትዮጵያ ህልውና እናረጋግጣለን ብሏል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.