Fana: At a Speed of Life!

አቃቤ ህግ እነ እስክንድር ነጋ የተከሰሱበትን የወንጀል ክስ አሻሽሎ አቀረበ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 19 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አቃቤ ህግ ፍርድ ቤት ባዘዘው ትዕዛዝ መሰረት እነ እስክንድር ነጋ የተከሰሱበትን ሃይማኖትና ብሄርን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት መፍጠር ወንጀል ክስን አሻሽሎ አቀረበ።
ባለፈው ቀጠሮ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት 1ኛ የህገ መንግስትና የጸረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት÷ የተከሰሱበት ክስ ተፈጸመ የተባለው ወንጀል የት ቦታ፣ በየትኛው ሰዓት፣ ክፍለ ከተማና ወረዳ እንዲሁም በተፈጸመው ወንጀል ደረሰ የተባለው የንብረት እና የሰው ጉዳት በዝርዝር ተሻሽሎ እንዲቀርብ በታዘዘው መሰረት ነው ተሻሽሎ የቀረበው።
የተሻሻለው ክስም እስክንድር ነጋን ጨምሮ ለአምስት ተከሳሾች የደረሳቸው ሲሆን÷ ችሎቱም የተሻሻለውን የክስ ጭብጥ ለችሎቱ ታዳሚዎች በንባብ አሰምቷል።
በዚህም መሰረት በቦሌ ክፍለ ከተማ ደረሰውን የንብረት ውድመት እንዲሁም በኮልፌ፣ በንፋስ ስልክ እና በሌሎችም ክፍለ ከተሞች የደረሰውን የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት ውድመትን አሻሽሎ በተናጥል አቅርቧል።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ግን የሰው ሕይወት አለመጥፋቱን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ በክፍለ ከተማው በተፈጠረው ሁከትና የእርስ በርስ ግጭት ተሳትፎ አለው ተብሎ በ5ኛ ተራ ቁጥር የተከሰሰው ጌትነት በቀለ የተከሰሰበት ወንጀል ዋስትና አያስከለክለውም ብሏል።
በዚህም ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ የ30 ሺህ ብር የገንዘብና የሰው ዋስ አስይዞ ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል በመፍቀድ ከሀገር እንዳይወጣም ገደብ ጥሎበታል።
ሌሎች ተከሳሾች ግን በተከሰሱበት ወንጀል የ14 ሰው ህይወት የጠፋበት ነው ያለው ፍርድ ቤቱ ይህም ዋስትና ያስከለክላል ብሏል።
በመሆኑም ተከሳሾቹ ባሉበት ማረሚ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ በማለት የዋስትና ጥያቄያቸውን ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጓል።
ችሎቱ ጠበቆቻቸው የክስ መቃወሚያቸውን መስከረም 29 በጽህፈት ቤት እንዲያስገቡ ያዘዘ ሲሆን÷ አቃቤ ህግም መስከረም 29 መቃወሚያቸውን ተቀብሎ ለጥቅምት 12 በችሎት እንዲያቀርብ ሲል ተለዋጭ ቀጠሮ ፍርድ ቤቱ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.