Fana: At a Speed of Life!

አትሌት ሰምበሬ ተፈሪ በድሬዳዋ በተካሄደው 14ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር አሸነፈች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 14፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌዴራል ማረሚያ ቤትን በመወከል የተወዳደረችውአትሌት ሰምበሬ ተፈሪ በድሬዳዋ በተካሄደው 14ኛው የኢትዮጵያ ግማሽ ማራቶን ውድድር አሸንፋለች፡፡

ዓለም አቀፍ ዝና ያላቸው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተሣተፉበትና ዛሬ በድሬዳዋ ከተማ በተካሄደው ግማሽ ማራቶን ውድድር በኦሮሚያ ክልልና በኦሮሚያ ፖሊስ ክለብ የበላይነት ተጠናቋል፡፡

ስፖርት ለአገር ዕድገትና ብልጽግና እንዲሁም ለአገር ገጽታና አንድነት እንዲውል በስፖርት መሠረተ-ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ የድሬዳዋ አስተዳደር አስታውቋል፡፡

መነሻውን በብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት አድርጎ የድሬዳዋን ዋና ዋና ጎዳናዎች ባካለለው የግማሽ ማራቶን ውድድር ላይ 5 ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች፣ 14 ክለቦችና የግል ተወዳዳሪ ተካፍለዋል፡፡

በሴቶች በተደረገው ውድድር ሰምበሬ ተፈሪን በመከተል የኤልሚ አለንዶ ክለብ ተወዳዳሪ ህይወት ገብረኪዳን ሁለተኛ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ፈታው ዘራይ ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

በወንዶቹ ምድብ ደግሞ ከሶስት አመት በፊት በአፍሪካ ሻንፒዮን 2ተኛ የወጣው የኦሮሚያ ፖሊስ ክለብ አትሌት ሉኡል ገብረየስ በበላይነት ሲያጠናቅቅ የክለብ አጋሩ ሲሳይ ለማ ሁለተኛ እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ በላይ ጥላሁን ሶስተኛ በመሆን ውድድሩን ጨርሰው የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳሊያ ወስደዋል።

በውድድሩ ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ለወጡት ከ25 ሺህ ብር እስከ 6 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የዘንድሮውን 14ኛው የኢትዮጵያ የግማሽ ማራቶን ውድድር በሴቶች ዘርፍ በቡድን 40 ነጥብ በማምጣት ኦሮሚያ ክልል አንደኛ በመውጣት የዋንጫ አሸናፊ ሲሆን በወንዶች ደግሞ በ29 ነጥብ የኦሮሚያ ፖሊስ ክለብ ግንባር ቀደም በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ሆኗል፡፡

ለአሸናፊዎቹ ዋንጫ የሸለሙት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ አስተዳደር ንግድ ኢንዱትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሃር እንደተናገሩት፤ ስፖርትን ለአገር ብልጽግናና ለሀገር ገጽታ ግንባታ ለማዋል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

ለወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችና መሰረተ-ልማቶች ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ስፖርትን መደገፍና ማሳደግ ወጣቱን ከአልባሌ ስፍራዎች መጠበቅ ብቻ ሣይሆን የአገር ብልጽግና ማሳኪያ ጎዳና እንደሆነም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡-https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.