Fana: At a Speed of Life!

አቶ ልደቱ አያሌው በቀረበባቸው ህገ መንግስቱን ለመናድ በማሰብ የሽግግር መንግስት ሰነድ በማዘጋጀት ወንጀል ክስ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያን አሰሙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አቶ ልደቱ አያሌው በቀረበባቸው ህገ መንግስቱን ለመናድ በማሰብ የሽግግር መንግስት ሰነድ በማዘጋጀት ወንጀል ክስ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያን አሰሙ፡፡

ክሱ በኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምስራቅ ምድብ ወንጀል ችሎት ዛሬ በንባብ ቀርቧል፡፡

በክሱ ላይም አቶ ልደቱ አያሌው እና አራት ጠበቆቻቸው መቃወሚያ አሰምተዋል፡፡

በመቃወሚያቸው ክሱ ተገቢነት የሌለው እና በህገ መንግስቱ የተሰጣቸውን የመናገር እና የመፃፍ መብታቸውን የሚቃረን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የክሱ አንቀፅ እንደ አጠቃላይ እንደ ፖለቲከኛ ወይም እንደ ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ የሽግግር መንግስት ሰነድ ሃሳባቸውን ያቀረቡት፤ ለመገናኛ ብዙሃንም ሆነ ለህዝብ ውይይት የቀረበ እንጂ ህገ መንግስቱን በሃይል ለመናድ ታስቦ አለመሆኑን ጠበቆች በመከራከሪያ ነጥቦቻቸው አንስተዋል፡፡

አቶ ልደቱ በበኩላቸው ሰነዱ ለሃገሪቱ ሰላማዊ ትግል እንዲሁም አሁን ላለው መንግስት በጠቃሚነት የቀረበ እንጅ መንግስትን በሃይል ከስልጣን ለማውረድ የተዘጋጀ አይደለም፤ ሁለተኛውም ቢሆን በረቂቅ ላይ የሚገኝ እና ያልታተመ መሆኑን በመጥቀስ ሌሎች ፓርቲዎች ይህን ሰነድ የራሳቸው አድርገው አቅርበዋል ብለዋል፡፡

በዚህም እኔ በዚህ ሰነድ ባለቤት ተደርጌ መከሰሴ ተገቢነት የለውም ሰነዱም ቢሆን በሃሳብ ደረጃ ያለ እንጂ በመንግስት ላይ ያደረሰው ጉዳትም ሆነ ሊያደርስ የሚችለው ምንም ዓይነት ጉዳት እንደሌለም አመላክተዋል፡፡

የሽግግር መንግስት ሰነዱ አማራችጭ ረቂቅ ሃሳብ ነው፤ ይህም ማለት ቢሻሻል፣ ቢቀየር አስፈላጊ ከሆነም ሊቀየር የሚችል አማራጭ ሃሳብ ነው ፤ መንግስት የሃገሪቱ ፖለቲከኞች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳብ አቅርቡ ሲል የቀረበ ነው ሲሉም ተከራክረዋል፡፡

ሰነዱም ለውይይት እና ለክርክር የቀረበ ነው ሲሉ ባለፉት 20 ዓመታት ህጋዊ እና ሰላማዊ ሆነው ሲታገሉ እንደነበር ተናግረዋል፡፡
እንደ አጠቃላይ ህገ መንግስቱ በሰጣቸው መብት ሃሳባቸውን በመፃፋቸው መጠየቅ ወይም መከሰስ እንደሌለባቸውም ነው የተናገሩት፡፡

ጠበቆቻቸው በኦ ኤም ኤን ቀርቧል የተባለው ይህ ሰነድ በማስረጃነት መያዙ ተገቢነት የለውም ፤ የህግ አግባብን የተከተለ አይደለም በማለትም ነው የተከራከሩት፡፡

ከሳሽ ዐቃቤ ህግ በበኩሉ የተከሰሱት የወንጀል ህግ 256ን በመተላለፍ ሲሆን ማስረጃውም ቢሆን እንደ አስፈላጊነቱ ከክሱ ጋር እንደሚቀርብ ጠቅሶ የሽግግር መንግስት ሰነዱ መንግስትን በሃይል ከስልጣን ለማውረድ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ሲል መቃወሚያው ላይ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

የክሱን ተገቢነት የገለፀው ዐቃቤ ህግ የሃገሪቱን ህግ ተላልፈው የተገኙ በመሆኑ ወንጀል ፈፅመዋል ተብሎ እንጅ የተከሰሱት የግል ሃሳብን የማቅረብ መብትን ለመገደብ አይደለም ሲል ምላሽ ሰጥቷል፡፡

በዚህ መልኩ የመጀመሪያ ደረጃ ክስ መቃወሚያ ከተሰማ በኋላ በጠበቆች በኩል የዋስትና ጥያቄ ቀርቧል፡፡

የአቶ ልደቱ አያሌው የልብ ቀዶ ጥገና ተከትሎ በህክምና ቀጠሮ ህክምና ባለማግኘታቸው ህይወታቸው አደጋ ላይ እንዳለ በመጥቀስ እና ለዚህም ማሳያ የሃኪም ማስረጃ በፅሁፍ አቅርበዋል፡፡

አቶ ልደቱም ፍርድ ቤቱን የፍርድ ሂደት ለመከላከል በህይወት መኖር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው አሁን ባሉበት የልብ የሰው ሰራሽ መሳሪያ በማንኛውም ሰዓት ህይወታቸውን አደጋ ላይ እንደሚጥል ገልፀው በዋስ ወጥተው ህክምናቸውን አድርገው እንዲመለሱም አመላክተዋል፡፡

ዐቃቤ ህግም ዋስትናውን በመቃወም ወጥተው ላይመለሱ ይችላሉ ሲል ስጋቱን ገልጿል፡፡

ትዕዛዝ እስከሚሰጥ ድረስም በማረሚያ ቤት ይቆዩልኝ ሲል የጠየቀ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ አሁን ካላቸው የጤና ሁኔታ አንጻር ባሉበት እንዲቆዩ በማለት ዋስትናው ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት እና አጠቃላይ ብይን ለመስጠት ለጥቅምት 20 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በታሪክ አዱኛ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.