Fana: At a Speed of Life!

አቶ ስብሃት ነጋ እና ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) አቶ ስብሃት ነጋ፣ ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ አምባሳደር አባይ ወልዱን ጨምሮ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡

ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት ያቀረበው የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ሲሆን ተጠርጣሪዎቹ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ነው የቀረቡት፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ችሎት የቀረቡት የዐቃቤ ህግ የቅድመ ምርመራ ምስክርን ለመስማት በተሰጠ ተለዋጭ ቀጠሮ ነው፡፡

ዐቃቤ ህግ ባሳለፍነው ሳምንት 50 ምስክሮች ማዘጋጀቱን መግለጹን ይታወሳል፡፡

በዚሁ ችሎት የነስብሃት ጠበቆች ማረሚያ ቤት ሄደን መግባት አልቻልንም ከፍርድቤት ጥብቅና ፍቃዳችሁን አቅርቡ ብለውን ተመልሰናል ባልተመካከርንበት ሁኔታ ምስክርመሰማቱ ተገቢ ስላልሆነ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን ብለዋል፡፡

አምባሳደር አባይ ወልዱ አይናቸው እየተጋረደ ስለሆነ በግል እንዲታከሙ ይታዘዝ፤ አቶ ስብሃት በግል እንዲታከሙ የታዘዘው ትዕዛዝ ተፈጻሚ አልሆነም የሚል አቤቱታ አሰምተዋል፡፡

ተጠርጣራዎቹ ከቤተሰብ ምግብ ቅዳሜና እሁድ ብቻ እንደሚገባላቸው በመጥቀስ፥ ከሰኞ እስከ አርብ እንዲፈቀድ ትዕዛዝ ይሰጥልንም ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም የተጠርጣሪዎቹ ቁጥር ብዙ መሆኑን በመጥቀስም እድሜያቸው የገፉና ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው ስላሉ ለኮሮና እንዳይጋለጡ ታሳቢ ቢደረግ ሲሉም አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

ዐቃቤ ህግም የተነሱ አቤቱታዎች ተገቢነት የሌላቸውና ጠበቆችም ባለፈው ሳምንት ተጠርጣሪዎችን ማግኘት ይችሉ ነበር በማለት ጉዳዩ በጠበቆቹ ቸልተኝነት የመጣ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ይህ የቅድመ ምርመራ ምስክር በመሆኑም በአፋጣኝ ማስረጃ ለማቆየት ምስክር መሰማት እንዳለበት በመጥቀስ፥ በጠበቆች የተነሳው አቤቱታ ጉዳዩን ለማዘግየት በማሰብ ነው በሚል አቤቱታውን ተቃውሟል፡፡

ጉዳዩን የተከታተለው ችሎቱ ጠበቆቹ ስነምግባር በጎደለው እና የችሎቱን ክብር ባልጠበቀ መልኩ ተከራክራችኋል በሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡

በተነሱ አቤቱታዎች ላይ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት በይደር ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

በታሪክ አዱኛ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.