Fana: At a Speed of Life!

አቶ ሽመልስ አብዲሳ በኦሮሚያ ክልል የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 25 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከተቋቋመው ኮሚቴ ጋር በፅህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

የክልሉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሳይዛባ ህብረተሰቡ ስለኮሮና ቫይረስ ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኝ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።

በተለይም ፋብሪካዎች ሠራተኞቻቸውን ከቫይረሱ መከላከል በሚችሉበት ሁኔታ ሥራቸውን ማከናወን አለባቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ አርሶ አደሩም የልማት ሥራውን በጀመረበት መንገድ ሊቀጥል እንደሚገባ መክረዋል።

በትራንስፖርት ዘርፍ በከተሞች ውስጥ የሚደረግ የታክሲ እንቅስቃሴ እንዲሁም ከአንድ ከተማ ወደ ሌላ ከተማ የሚደረግ የህዝብ ትራንስፖርት እንዲቆም መወሰኑንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል።

በክልሉ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የተቋቋመው ኮሚቴም እስካሁን ለ9 ሚሊየን ሰዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት በገጽ ለገጽ መሰጠቱን አስታውቋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረትም 144 ሺህ በጎ ፈቃደኞች ነፃ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ብሏል ኮሚቴው።

እስካሁን ቫይረሱን ለመከላከል ተግባር የሚውል 46 ሚሊየን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንም ኢዜአ ዘግቧል።

በክልሉ እስካሁን 44 የለይቶ ማቆያ ቦታዎች፣ 107 ሆስፒታሎች፣ 174 ጤና ጣቢያዎች፣ 677 አልጋዎች እና 23 አምቡላንሶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ዝግጁ መሆናቸው ተገልጿል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.