Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት አምባሳደሮች በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ ገለፃ አደረጉ

አዲስ አበባ ፣ የካቲት 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አምባሳደሮች እና ተወካዮች በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ  ገለፃ አድርገዋል።

አቶ ደመቀ መንግስት በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትን ለሟሟላት በሙሉ አቅሙ መንቀሳቀሱን በመግለፅ ህግን የማስከበር እርምጃው በስኬት ከተጠናቀቀ ጀምሮ ከፍ ያለ መሻሻል እያሳየ መምጣቱን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ጨምሮ ለሰብዓዊ ድጋፍ የሚያደርጉ አካላት ያለገደብ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ፈቃድ እንደተሰጠም ጠቁመዋል።

ለሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪዎች የአሰራር እንቅፋቶች በመቀረፉ በክልሉ ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ እንዲሳተፉ መደረጉንም አብራርተዋል፡፡

በክልል ስለተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በጋራ ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ለአምባሳደሮቹና ተወካዮቹ ገለፃ አድርገዋል።

አምባሳደሮቹና ተወካዮቹ በበኩላቸው መንግስት የሰብዓዊ ሁኔታ እና የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ለማሻሻል የወሰደውን እርምጃ በማድነቅ አንዳንድ ጋዜጠኞች እና ተርጓሚዎች ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች አንስተዋል።

አቶ ደመቀ ለተሳታፊዎቹ በሰጡት ምላሽ በክልሉ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ዜጎች የሰብዓዊ ድጋፍ እየተደረጋላቸው መሆኑን እና በህወሓት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ የመገንባት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም መንግስት በ40 ቢሊየን ብር በክልሉ ሰብአዊ ድጋፍ ማድረሱን ጠቅሰው፥ ይህም 70 በመቶውን ድርሻ እንደሚይዝም አስረድተዋል፡፡

መንግስታት እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶች በፍጥነት እና ቀጣይነት ባለው መንገድ በቂ ሀብቶችን በማሰብሰብ በክልሉ ሰብአዊ ድጋፎችን ለማድረስ ለተቋቋመው ግብረ ሀይል እንዲያቀርቡም ጥሪ አቅርበዋል።

ጋዜጠኞች በክልሉ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ዘገባ እንዲሰሩ ፈቃድ መሰጡትን የገለፁት አቶ ደመቀ ባለፉት ቀናት ታስረው የነበሩት ከእስር መለቀቃቸውን ተናግረዋል።

አቶ ደመቀ መንግስት ያለምንም ድካም ችግሮችን እና ጥቂት እንቅፋቶችን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ሙያዊ የስራ ስነ ምግባራቸውን ሊያከብሩ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.