Fana: At a Speed of Life!

አቶ ደመቀ መኮንን ከስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በስልክ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ጥር 19፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ከስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አን ሊንዲ ጋር በሁለትዮሽ እና ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የስልክ ውይይት አካሂደዋል።

በወቅቱም አቶ ደመቀ መኮንን መንግስት በወሰዳቸው አዎንታዊ እርምጃዎችን በተመለከተ በተለይም እስረኞችን ክስ በማቋረጥ የመፍታት ውሳኔ እና ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ ምክክር ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት የተጠናቀቀ ስለመሆኑም ለሚኒስትሯ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አክለውም በመንግስት በትግራይ ሰራዊቱ እንዳይገባ ቢወስንም የህወሃት የሽብር ቡድን በአባላ በኩል ጥቃት በመከፈት በትግራይ ክልል የሚደረገው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ተደራሽ እንዳይሆን እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ ስዊድን ለያዘችው ሚዛናዊ አቋም ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

አን ሊንዲ በበኩላቸው መንግስት እስካሁን የወሰዳቸውን አበረታች የሰላም እርምጃዎች አድንቀው፤ ይህም ለዘላቂ ሰላም መስፈን ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተስፋቸውን ገልጸዋል።

አክለውም ሀገራቸው በኢትዮጵያ ለልማት ፕሮጀክቶች የምትሰጠውን ድጋፍ የምትቀጥል መሆኑን ገልጸው፤ በሚካሄደውን ሁሉን አቀፍ የብሔራዊ ምክክር ሀገራቸው የምትደገፍ መሆኑን ከሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.