Fana: At a Speed of Life!

ሩሲያ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚደረግን ጣልቃ ገብነት እንደማትደግፍ ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ ገላፃ አድርገውላቸዋል፡፡

በትግራይ ክልል ህግን የማስከበር እርምጃ ተከትሎ የመልሶ ማቋቋም፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ ድጋፍ፣ ለመገናኛ ብዙሃን ሽፋን እንዲሰጡ ማመቻቸት እንዲሁም ከሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ጋር የሚነሱ ውንጀላዎችን የማጣራት ተልዕኮ እና ህጋዊ እርምጃዎችን የመውሰድ ተግባራት በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስድስተኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ክዋኔ አስመልክቶ ሰላማዊ በሆነ መልኩ መጠናቀቁን እና በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ መርሃ ግብር መሰረት የድምፅ ቆጠራ ውጤቶች ለህዝብ ይፋ እየተደረጉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቁዎችን ኢትዮጵያ አሁንም አፍሪካዊ ችግሮችን አፍሪካዊ መፍትሄ የመስጠት አካሄድን በመከተል በፍትሃዊነት ላይ የተመሰረተ አቋሟን አጥብቃ እንደምትቀጥል አስረድተዋል፡፡

ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ግጭት በሁለቱ ሃገራት መካከል ችግሮችን በጋራ መፍቻ ስርዓት የተበጀ ቢኖርም፤ ሱዳን አጋጣሚን ተጠቅማ ወደ ኢትዮጵያ ግዛት መግባቷ ከዓለም-አቀፍ ስርዓት ውጪ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ከሱዳን ጋር ያለውን የድንበር ግጭት በዲፕሎማሲ ጥረት መፍትሄ ለማበጀት ኢትዮጵያ የጀመችው ጥረት በቀጣይ ተጠናክሮ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት ራሺያ እንደቀድሞ ሁሉ በመርህ እና የሃገር ሉዓላዊነትን ባከበረ መልኩ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ እና የምትወስደውን አቋም ያደነቁ ሲሆን፤ ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዕምነታቸውን አስቀምጠዋል፡፡

በተጨማሪ በቀጣይ ዓመት የአፍሪካ-ራሺያ ፎረም አዲስ አበባ እንዲካሄድ በኢትዮጵያ በኩል ዝግጁ መሆኗን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ አረጋግጠዋል፡፡

ከሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ሰርጌ ላቭሮቭ በበኩላቸው፣ በትግራይ ክልል መንግስት በሃላፊነት የወሰደቻቸው እርምጃዎች እና በቁርጠኝነት የሚያከናውናቸው የሰብዓዊ ድጋፍ ተግባራት የመንግስትን የሞራል ፅናት እና የፖለቲካ ብቃት ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡

ስድስተኛው ሃገር አቀፍ ምርጫ ሩሲያ በታዛቢነት እንድትሳተፍ መደረጉ የታሪካዊ ግንኙነቱ ከፍታን ያንፀባረቀ መሆኑን በመጠቆም፣ ምርጫው በሰላማዊ ሁኔታ ስኬታማ ሆኖ መጠናቀቁ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡

በታላቁ ህዳሴ ግድብ በአፍሪካ ህብረት አመቻችነት የተጀመረው ድርድር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ሩሲያ እንደምታምን፤ ለዚሁም አስፈላጊውን የቴክኒክ ድጋፍ ለመስጠት ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል፡፡

ከሱዳን ጋር ያለው የድንበር ግጭት ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን በሰላማዊ መንገድ ለማስከበር እና ችግሮችን በዲፕሎማሲ ለመፍታት የምትከተለውን ጤናማ አካሄድ ማድንቃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የሚደረገውን ማንኛውም ጣልቃ ገብነት ሩሲያ እንደማትደግፍ ገልፀው፤ በሁለቱ ሃገሮች መካከል ያሉ የትብብር መስኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡

በተጨማሪ በቀጣይ ዓመት የአፍሪካ-ሩሲያ ፎረም በአፍሪካ ህብረት መዲና አዲስ አበባ እንዲካሄድ በኢትዮጵያ በኩል ዝግጁ መሆኗ መገለፁን አድንቀዋል፡፡

በሁለትዮሽ ግንኙነቱ በተለይ በትምህርት፣ በአቅም ግንባታ፣ በሳይንስ እና ቴክኖሊጂ አጠናክረው ለማስቀጠል፤ የተፈረሙ ስምምነቶች ወደ ተግባር ለማስገባት እንዲሁም በሂደት ላይ ያሉ ስምምነቶችም በፍጥነት እንዲፈረሙ ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል የቆየው ታሪካዊ ግንኙነት ትርጉም-ባለው ደረጃ በተለያዩ ዘርፎች ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን ሚኒስትሮቹ አረጋግጠዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.