Fana: At a Speed of Life!

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከስፔኗ አቻቸው ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከስፔኗ አቻቸው አራንቻ ጎንዛሌዝ ጋር በስልክ ተወያዩ።

ሚኒስትሮቹ የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች እና የኮቪድ 19 ወረርሽኝን በትብብር መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ነው የተወያዩት።

በውይይታቸውም ሁለቱ ሃገራት ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እና ኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል በትብብር ለመስራት ተሰማምተዋል።
አቶ ገዱ ስፔን በሁለትዮሽ እና በአውሮፓ ህብረት በኩል ለኢትዮጵያ እያደረገች ላለው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት በመላው ዓለም እየጠፋ ባለው የሰው ህይወት የተሰማቸውን ሀዘንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የኮቪድ ወረርሽኝን ለመግታት እያደረገች ያለውን ጥረት በተመለከተ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፥ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ እንዲሁም ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን እስከዛሬ ድረስ ያረደጓቸውን ውይይቶች በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የስፔን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አራንቻ ጎንዛሌዝ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ስለተደረገላቸው ገለጻ አመስግነዋል።

ስፔን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር እንደምትሰራ ገልጸው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው ከመሆኑ ባሻገር ስለቫይረሱ ያልታወቁ በርካታ ጉዳዮች ስላሉ የሁሉም አካላት ትብብር በእጅጉ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የታላቁ የህዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ምን ማለት እንደሆነ እንደሚገነዘቡና ሶስቱ ሃገራት ልዮነታቸውን በውይይት መፍታት እንዳለበቸውም ጠቁመዋል።

የአባይ ወንዝ ቀጠናዊ ትብብርን በሚያመጣ መልኩ በትብብር መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ማለታቸውንም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.