Fana: At a Speed of Life!

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከኔዘርላንድስ የውጭ ንግድና ልማት ትብብር ሚኒስትር ጋር በስልክ ተወያዩ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከኔዘርላንድስ የውጭ ንግድ እና ልማት ትብብር ሚኒስትር ሲግሪድ አግነስ ማርያ ካግ ጋር በስልክ ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ፣ ክልላዊ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ፥ የኢትዮጵያና የኔዘርላንድስ ግንኙነት በጥሩ ሁኔታ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ግንኙነቱን በዓለም ላይ የተከሰተውን የኮሮና  ቫይረስ ወረርሽኝ እና በሌሎች ዘርፎች ይበልጥ ለማጠናከር ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸዋል።

አያይዘውም ኔዘርላንድስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመግታት በሚደረገው እንቅስቃሴ እያደረገች ላለው ድጋፍ ሚኒስትሩ አመስግነዋል።

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በዓለም ላይ በደረሰው የሰው ሞት የተማቸውን ሀዘን የገለጹ ሲሆን፥ ወረርሽኙን መቋቋም የሚቻለው በትብብር በመሆኑ ሁሉም አካላት ትብብሩን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተም ገለጻ ያደረጉት አቶ ገዱ፥ ወረርሽኙ ወደ ገጠር ተስፋፍቶ በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ በመንግስት እና በህዝብ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።

የኔዘርላንድስ የውጭ የንግድ እና ልማት ትብብር ሚኒስትር ሲግሪድ አግነስ ማርያ ካግ በበኩላቸው÷ ሀገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ባላት ግንኙነት ደስተኛ መሆናቸውን እና ሀገራቸው ይህንኑ አጠናክራ ለመቀጠል እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።

ወረርሽኙ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚው ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ኔዘርላንድስ ከአውሮፓ ህብረት እና ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅርበት እየሰራች መሆኑንም ገልጸዋል።

አያይዘውም የኮሮና ወረርሽኝ ዘር፣ ቀለም እና የቦታ ርቀት የማይገድበው በመሆኑ የሁሉንም አካላት ትብብር እንደሚጠይቅ ያነሱት  ሲግሪድ ካግ፤ ኔዘርላንድስ ወረርሽኙ የከፋ ጫና እንዳያሳድር በትኩረት እየሰራች መሆኗን ተናግረዋል።

 

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!

https://t.me/fanatelevision

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.