Fana: At a Speed of Life!

አየር መንገዱ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ጋር የአጋርነት ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ አየርመንገድ እና የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤይድ) ጋር የአጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

የአጋርነት ስምምነቱ የግብርና ውጤቶችን በሃገር ውስጥ ካለው አርሶአደር ለማግኘት ያለመ ነው ተብሏል፡፡

ስምምነቱን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማርያም እና በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር ተፈራርመውታል፡፡

አቶ ተወልደ በስምምነቱ ወቅት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ለአየር መንገዱ እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የአጋርነት ስምምነቱ አየር መንገዱ ለመንገደኞች ከፍተኛ ጥራት ያለው ምግብ እንዲያቀርብ ከማገዙም ባለፈ አርሶ አደሮቹን በገበያ ሰንሰለት ውስጥ በማስገባት ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት ያግዛልም ብለዋል፡፡

በስምምነቱ መሰረት የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች እና ምግብ አቅራቢዎች ቴክኒካዊ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ይሆናል፡፡
ከዚህ ባለፈም የአየር መንገዱን መስፈርት ባሟላ መልኩ ያዘጋጁትን ምግብ እንዲያቀርቡ እገዛ እንደሚያደርግላቸውም ተገልጿል፡፡

ስምምነቱም አርሶ አደሮችና በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ አካላት አዳዲስ የገበያ አማራጮችን እንዲያገኙ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ ይረዳል ተብሏል፡፡

ለአየር መንገዱ ደግሞ ለደንበኞቹ የምግብ ፍጆታነት የሚውሉና ትኩስ የግብርና ውጤቶችን እንዲያገኝ በማድረግ ከውጭ ሃገር የሚያስገባውን የተቀነባበሩ ምግቦች ለመቀነስ ይረዳዋል ነው የተባለው፡፡

በዚህም ከአርሶ አደሮች በተጨማሪ የገበሬዎች የህብረት ስራ ማህበራት፣ የወጣትና ሴቶች ማህበራትን ጨምሮ ሌሎች አካላትን በገበያ ሰንሰለት ውስጥ በማስገባት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ እንደሚረዳም ታምኖበታል፡፡

ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮችና አነስተኛ ንግድ አንቀሳቃሾች ከ1 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ማግኘታቸውን የአሜሪካ ኤምባሲ መረጃ ያሳያል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.