Fana: At a Speed of Life!

አደገኛ ዕፅ ስታዘዋውር የተገኘች የታይላንድ ዜጋ በቁጥጥር ስር ዋለች

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር አደገኛ ዕፅ ስታዘዋውር የተገኘችውን ታይላንዳዊት በቁጥጥር ስር አዋለ፡፡

በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል መከላከል ዘርፍ የኢንተለጀንስ አደገኛ ዕፅና ሬዲዮ መገናኛ ዳይሬክቶሬት ስር የሚገኘው የአደገኛ ዕፅ ቁጥጥር ምክትል ዳይሬክቶሬት ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር ትናንት ከምሽቱ አራት ሰዓት በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪዋን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል፡፡፡

ተጠርጣሪዋ ከአዲስ አበባ ወደ ታይላንድ ባንኮክ ጉዞ ማድረግ ላይ የነበረች ሲሆን እጅ ከፍንጅ መያዟን የአደገኛ ዕፅ ቁጥጥር ኦፕሬሽን ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር መንግስትአብ በየነ ገልጸዋል፡፡

የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዋ አደንዛዥ ዕፁን በልብስ ውጫዊ የሻንጣ አካል በመደበቅ ለማሳለፍ ሙከራ ብታደርግም ሁለቱ የፀጥታ አካላት ባደረጉት ክትትል ተጠርጣሪዋን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮማንደሩ ተናግረዋል፡፡

በእጇ የተገኘው 2 ነጥብ 6 ኪሎ ግራም የሚመዝን ኮኬይን የተሰኘ አደገኛ ዕፅ መሆኑን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.