Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል ተማሪዎች ከግቢ እንዳይወጡ ከለከለ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ተማሪዎች ከግቢ እንዳይወጡ መከልከልን ጨምሮ ሌሎች ውሳኔዎችን አሳለፈ።

ዩኒቨርሲቲው ዛሬ በድረ-ገጹ እንዳስነበበው የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል 14 የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳልፏል።

በዚህም ማንኛውም ተማሪ ከግቢ መውጣት አይችልም፤ ከወጣም ተመልሶ መግባት እንደማይችል ወስኗል።

ማንኛውም ተማሪ ከከተማ ወደ ግቢ መግባት የተከለከለ ሲሆን አስፈላጊውን ምርመራ አድርጎ ከቫይረሱ ነጻ መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ መግባት እንደሚችልም አስቀምጧል።

በግቢው ውስጥ የካፌ ተገልጋይ ያልሆኑ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች አስፈላጊውን ክፍያ በመፈጸም አገልግሎት የሚያገኙ ሲሆን ይህን ካላደረጉ ግቢውን ለቀው ይወጣሉ።

ዩኒቨርሲቲው ስፖርታዊ ጨዋታዎችን፣ ተሰብስቦ ቴሌቪዥንና ዲኤስቲቪ መመልከትንም ከልክሏል።

በኢ-ሜይል እና ኦንላይን ትምህርት መስጠት የሚቀጥል ሲሆን ተማሪዎች በቤታቸውና ዶርሚተሪያቸው ሆነው ትምህርታቸውን ይከታተላሉ።

መምህራንም ከመጋቢት 15 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ዩኒቨርስቲው ግቢ ሳይመጡ የኢ-ሜይል እና ኦንላይን ትምህርቶች በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ይሰጣሉ።

በዩኒቨርሲቲው ግቢ ውስጥ የሚገኙ ሙዚየሞችና ኦቭዘርቫቶሪዎች ዝግ የሚሆኑ ሲሆን ጎብኝዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው መግባት እንደማይችሉ ባሳለፈው ውሳኔ አስቀምጧል።

አዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከላይ የተዘረዘሩትንና ሌሎች ውሳኔዎችን ያሳለፈ ሲሆን በአገሪቱ በሚኖረው ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ውሳኔዎችን የሚሻሻል መሆኑን ማስታወቁን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.