Fana: At a Speed of Life!

አዲስ ወግ የውይይት መድረክ በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተካሄደ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 24 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) አዲስ ወግ የውይይት መድረክ በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት ተካሄደ።

የውይይት መድረኩ “ከታሪክ ምን እንማር? በስነልቦና እንዴት እንጠንክር?” በሚል ርዕስ ነው የተካሄደው።

በውይይቱ ላይ የተለያዩ ምሁራን ያጋጠሙ ችግሮችን መፍታት የሚቻልባቸውን አግባቦች በተመለከተ ተወያይተዋል።

ምሁራኑ ከታሪክ አንጻር ያጋጠሙ ክስተቶች የተነሱ ሲሆን፥ እነዚህን አጋጣሚዎች ለመፍታት የተደረጉ ጥረቶች፣ ያጋጠሙ ችግሮችና መልካም አጋጣሚዎች ላይም ሃሳብ አንስተዋል።

ወረርሽኞች ሲከሰቱ የሚያስከትሉትን ሁለንተናዊ ቀውስ በተመለከተም ምሁራኑ ውይይት አድርገዋል።

በዚህም ማህበራዊ ቀውስ፣ የስነ ልቦና ጫና፣ ጭንቀት እና ፍርሃት እንደሚያስከትሉም በውይይታቸው ጠቅሰዋል።

ኮቪድ19ን ለመከላከልም አዳዲስ አስተሳሰቦችን ማጎልበት ይገባል ብለዋል ምሁራኑ።

በመድረኩ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል መሠረታዊ የባሕሪ ለውጥ ማምጣትና የመከላከል ጥረትን እንደሚጠይቅ የተነሳ ሲሆን፥ ምሁራኑም አሁን ላይ ከተከሰተው የኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ይበጃሉ ያሏቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ሰንዝረዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር አበባው መንፈሳዊ ጥንካሬን ለማግኘት አብዝቶ በመጸለይ ፈጣሪን መማፀን እና እንደ ሰርግና እድር ያሉ ማህበራዊ መስተጋብሮችን ማቋረጥ አስፈላጊ ስለመሆኑ ሃሳብ ሰንዝረዋል።

መሰል ሁኔታዎች ወረርሽኝ በሚከሰትበት ወቅት ለማስፋፋት ከሚኖራቸው ሚና አንጻር ማቋረጡ ተገቢ ነው ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአዕምሮ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ቢኒያም ወርቁ ደግሞ፥ በወረርሽኝ ወቅት ማህበራዊ ከለላ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ኮቪድ19 ዕድሜያቸው በገፋና ተጓዳኝ ህመም ባለባቸው ሰዎች ላይ እንደ መበርታቱም ለእነዚህ ሰዎች ልዩ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ባርኮት ሚልኪያስ በበኩላቸው፥ ኮቪድ19ኝን ለመግታት ልማዳዊ አሰራርን መቀየር እንደሚገባ አውስተዋል።

ችግሮችን መለየትና ወደ መፍትሄ መግባት ይገባል ያሉት ዶክተር ሚልኪያስ፥ ትናንሽ የሚባሉ ማሻሻያዎችን ማድረግና መፍትሄዎችን ማመላከት ተገቢ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል።

በመድረኩ የታሪክ መምህርና የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአዕምሮ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ባርኮት ሚልኪያስ፣ ዶክተር ታምራት ሃይሌ የታሪክ መምህር እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የአዕምሮ ህክምና ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ቢኒያም ወርቁ ተሳትፈዋል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.