Fana: At a Speed of Life!

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በፀጥታ ተቋማት ላይ የተከናወነው ሪፎርም ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በፀጥታ ተቋማት ላይ የተከናወነው የሪፎርም ስራ ተጨባጭ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን የመከላከያ ሠራዊት ህብረት ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን ገለጹ።
ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን ይህን ያሉት የመከላከያ ዋር ኮሌጅ “የፀጥታ አካላት ለውጥና የሲቪል ወታደራዊ ግንኙነት ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች” በሚል ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ነው።
በውይይቱ ጀነራል መኮንኖች፣ የክልልና የፌደራል የፀጥታ አመራሮች፣ ሚኒስትሮች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እና የቀድሞ ጦር ሠራዊት አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡
ሌተናል ጀነራል ይመር መኮንን እንደገለጹት÷ በኢትዮጵያ የተጀመረውን ለውጥ ተከትሎ የፀጥታ አካላትን ከፖለቲካዊ አመለካከትና ወገንተኝነት ነጻ ያደረገ እና የአገርን ጥቅም ያስቀደመ የፀጥታ ተቋማት ሪፎርም ተካሂዷል፡፡
የአገሪቱን ወቅታዊ የፀጥታና ደህንነት ስጋቶች ታሳቢ ያደረገ ጥልቅ የለውጥ ስራ መከናወኑን ጠቅሰው÷ በስልጠና እና አደረጃጀት የጸጥታ ተቋማት ጠንካራ እንዲሆኑ መደረጉንም አመላክተዋል፡፡
በህግ ማስከበርና በህልውና ዘመቻ ወቅት የተመዘገበው አመርቂ ድል በፀጥታ ተቋማቱ ላይ የተከናወነውን የሪፎርም ስራ ስኬታማነትን በግልጽ እንደሚያሳይ አብራርተዋል፡፡
ሁሉም የፀጥታ ተቋማት በቀጣይ ከፖለቲካዊ ወገንተኛነት ነፃ በሆነ መልኩ የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነት ለማስከበር መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የጥላቻ ትርክቶችን በማህበረሰቡ ውስጥ እየቆሰቆሱ ግጭት በመፍጠር አገር ለማተራመስ በሚሰሩ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.