Fana: At a Speed of Life!

አጣሪ ጉባኤው ምርጫን በተመለከተ ለቀረበለት ጥያቄ የውሳኔ ሀሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አቀረበ

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ከኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከኮቪድ-19 ጋር ተያይዞ ምርጫን በወቅቱ ማካሄድ ባለመቻሉ እንዲሁም የምክር ቤቶቹንና እና የአስፈፃሚ አካላትን የስራ ዘመን አስመልክቶ የቀረበለትን የሕገ መንግስት ትርጉም ጥያቄ ዛሬ ግንቦት 21 ቀን 2012 ዓ.ም ምላሽ ሰጠ።

ጉባኤው ከምክር ቤቱ ጥያቄው ከቀረበለት ጊዜ ጀምሮ ጉዳዩን ከተለያዩ አቅጣጫዎች አንፃር መመርመሩን ገልጿል።

ውሳኔ ወይም የውሳኔ ሀሳብ ከመስጠቱ በፊት በአዋጅ ቁጥር 798/2005 አንቀፅ 9 መሰረት በሕገ መንግስት የትምህርት ዘርፍ የተሰማሩና ልምዱ ያላቸውን ባለሙያዎች፣ ሕገ መንግስቱን በማርቀቅ ሂደት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ተሳትፎ ያላቸውን ግለሰቦች፣ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን ተቋማት፡ የኢፌዴሪ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድን ሀሳብ ለሕብረተሰቡ ግልፅ በሆነ መንገድ በተለያዩ ሚዲያዎች በቀጥታ የቴሌቭዥን ስርጭት በማስተላለፍ በጉባኤውም ሆነ በሀገሪቱ ደረጃ የመጀመሪያ የሆነውን የመስማት ሂደት ማከናወኑን ነው ያመለከተው።

ከመስማት ሂደቱ ጎን ለጎን ጉባኤው ባደረገው ጥሪ መሰረት በፅሁፍ የቀረቡ በርካታ ሀሳቦችን እንደተመለከተ አስታውቋል።

በተጨማሪም ሀሳብ ለማጎልበት የሚረዱ ጥናቶችን በጉባኤው ፅህፈት ቤት ባለሙያዎች ያስጠና ሲሆን፥ እነዚህን መሰረት አድርጎ ጉባኤው ባስቀመጣቸው ዋና ዋና ጭብጦች ላይ ለሁለት ሳምንታት ያህል ተከታታይና ጥልቅ የሆነ ውይይት በማድረግ ምላሽ በማዘጋጀት የውሳኔ ሀሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ማቅረቡን ገልጿል።

ጉባኤው በምላሹ ላይ ሕገ መንግስቱን መሰረት በማድረግ የፍርድ ቤት ክርክርን አስታከው የመጡ ሕገ መንግስታዊ ሂደቶችን ብቻ ሳይሆን ሕገ መንግስታዊ የትርጉም ስርአትን ሊያሰፉ የሚችሉ አንኳር ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ትንተናና ብይን በመስጠት ጉባኤውም ሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግስቱ የተጣለባቸውን የሕገ መንግስት ትርጉም የማሳደግ ሀላፊነትንም ከግምት ውስጥ አስገብቻለሁ ብሏል።

ጉዳዩ ለጉባኤው ቀርቦ ፊት ለፊትም ይሁን በፅሁፍ የባለሙያዎችን አስተያየት ለመሰብሰብ በመወሰን ጥሪ ካቀረበበት ቀን ጀምሮ በተለያየ መንገድ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ሙያዊ ግዴታቸውን ተወጥተዋል ያላቸውን አካላት አመስግኗል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.