Fana: At a Speed of Life!

አጫጭር የዝውውር ዜናዎች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ የአውሮፓ እግር ኳስ ክለቦች በቀጣዩ የውድድር ዘመን ተጠናክረው ለመቅረብ በዝውውር ገበያው በስፋት እየተሳተፉ ነው።
ቀደም ሲል ኧርሊንግ ሃላንድን ከቦሩሲያ ዶርትመንድ ያስፈረመው የእንግሊዙ ሻምፒዮን ማንቼስተር ሲቲ÷ ኬልቪን ፊሊፕስን ከዮርክሻየሩ ክለብ ሊድስ ዩናይትድ በዛሬው ዕለት አስፈርሟል።
ክለቡ የአማካዩን ዝውውር በ45 ሚሊየን ፓውንድ በስድስት ዓመት የኮንትራት ውል አጠናቋል።
በሌላ በኩል የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ጋብርኤል ጀሰስን ከማንቼስተር ሲቲ በ45 ሚሊየን ፓውንድ አስፈርሟል።
ቀደም ሲል ፈረንሳዊውን አጥቂ አሌክሳንደር ላካዜትን ያሰናበተው አርሰናል ብራዚላዊውን አጥቂ በአምስት ዓመት ኮንትራት ነው ያስፈረመው።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ራሱን እያጠናከረ ያለው አርሰናል÷ ቀደም ሲል ከፖርቶ የአጥቂ አማካዩን ፋቢዮ ቪየራን ጨምሮ ሦስት ተጫዋቾችን ማስፈረሙ ይታወሳል።
አንጋፋ ተጫዋቾቹን በነጻ የለቀቀው የላንክሻየሩ ማንቼስተር ዩናይትድ÷ በአንጻሩ የቀድሞውን የቶተንሃም እና ኢንተር ሚላን አማካይ ክርስቲያን ኤሪክሰንን ለማስፈረም መስማማቱ ታውቋል።
ዴንማርካዊው አማካይ በላንክሻየሩ ክለብ የሦስት ዓመታት የኮንትራት ውል ለመፈረም በመርህ ደረጃ መስማማቱን ስካይ ስፖርት ዘግቧል።
በተያያዘም ማንቼስተር ዩናይትድ ታይሬል ማላቺያን ከፌይኖርድ በ13 ሚሊየን ፓውንድ ለማስፈረም የተስማማ ሲሆን÷ ተጫዋቹም የህክምና ምርመራውን ለማድረግ ማንቼስተር መድረሱን ዘገባዎች አመላክተዋል፡፡
በሌላ በኩል ክለቡ አርጀንቲናዊውን ተከላካይ ሊሳንድሮ ማርቲኔዝን ከአያክስ ለማስፈረም መጀመሪያ ካቀረበው የተሻለ የዝውውር ገንዘብ ማቅረቡም ተሰምቷል።
ተከላካዩን ለማስፈረም ከማንቼስተር በተጨማሪ አርሰናል ፍላጎት ያሳየ ሲሆን፥ አያክስ ለተጫዋቹ ዝውውር 43 ሚሊየን ፓውንድ እንደሚፈልግ አስታውቋል።
የስፔኑ ክለብ ባርሴሎና ደግሞ ፍራንክ ኬሲን ከኤሲ ሚላን በነጻ አስፈርሟል።
የካታላኑ ክለብ በዝውውር መስኮቱ የተጫዋቹ ዋነኛ ፈላጊ እንደነበር ይታወሳል።
ተጫዋቹ በካምፕ ኑ ለአራት አመታት የሚያቆየውን ውል ተፈራርሟል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.