Fana: At a Speed of Life!

አፍሪካ በግብር ማጭበርበርና ስርቆት በየዓመቱ 89 ቢሊየን ዶላር ታጣለች – ተመድ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥናት እንዳሳየው ከሆነ አፍሪካ በግብር ማጭበርበርና ስርቆት በየዓመቱ 89 ቢሊየን የሚጠጋ ዶላር እንደምታጣ አስታወቀ፡፡

ይህም አፍሪካ በየዓመቱ ከውጭ አገራት ለልማት ከምትቀበለው እርዳታ እንደሚበልጥ ነው ተመድ በሪፖርቱ የገለጸው፡፡

ትናንት ይፋ የሆነው ሪፖርት 248 ገፆችን የያዘ ሲሆን የግብር ማጭበርበሩና ስርቆቱ ቀድሞ ከተተነበየው እንደሚልቅ ነው ያሳየው፡፡

ግማሽ ያህሉ ምዝበራ የተፈጸመው በወጪ ንግዶች በወርቅ፣ በአልማዝ እና በፕላቲንየም መሆኑን ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡

እንዲሁም መዝባሪዎቹ በውጭ አገራት ያገኙትን ትርፍ በሚሰውሩበት ወቅት የአዳጊ አገራትን የውጭ ምንዛሪ ክምችትና የግብር ይዞታቸው በእጅጉ እንደሚጎዳው አትቷል፡፡

የተመድ የንግድና የልማት ጉዳዮች ሴክሬታሪ ጀነራል ሙክሂሳ ኪትዪ እንደተናገሩት ህገወጥ የሆነው የፋይናንስ ስርዓት አፍሪካውያንን እየበዘበዘ ይገኛል ብለዋል፡፡

ይህም በአህጉሪቷ የሚገኙ ተቋማትን እምነት እንደሚያሳጣ እንዲሁም ግልጽነትና ተጠያቂነት ላይ ጥላ እንደሚያጠላበት ነው የተናገሩት፡፡

ሪፖርቱ አፍሪካ ለዓለም አበዳሪ መሆኗን የጠቀሰ ሲሆን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው የእርዳታ ጥገኛ የሆነችው አህጉር በምዝበራው አማካኝነት ለዓለም እሴት አቅራቢ ሆናለች ሲሉ ነው የገለጹት፡፡

በተቋሙ የአፍሪካ ጉዳዮች የፖሊሲና የምርምር ባለሙያ የሆኑት ጁኒየር ዳቪስ ሪፖርቱ መረጃ ካማጣቀስ አንጻር ውስንነቶች እንዳሉበትም ገልጸዋል፡፡

ምንጭ፡-አልጀዚራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.