Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያውያን ከቁርሳቸው ቀንሰው ለተፈናቃዮች ሊደርሱላቸው ይገባል-ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያውያን ከቁርሳቸው ቀንሰው ለተፈናቃዮች ሊደርሱላቸው እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለን ጨምሮ የሴት ሚኒስትሮች፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኀላፊዎች እና ባለሃብቶች በአሸባሪው የትህነግ ቡድን የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉበትን ሁኔታ ተመልክተዋል፡፡
ወይዘሮ ጥሩ መሐመድ በእርጅና ዘመናቸው በአሸባሪው ትህነግ ከመርሳ ተፈናቅለው በደሴ ከተማ በንጉስ ሚካኤል ትምህርት ቤት ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ወደ መጠለያ የገቡትም ከአሸባሪው ቡድን ህይወታቸውን ለማትረፍ ነው። ወይዘሮ ጥሩ ሀብት ንብረታቸውን በአሸባሪው ቡድን አጥተው በችግር ውስጥ በመሆናቸው ሁሉም ሊደርስላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።
አሸባሪው የትህነግ ቡድን በፈጸመው ወረራ ከዋግ ኸምራ፣ ከሰሜን ወሎ፣ ከደቡብ ወሎ አራት ወረዳዎችና ከአፋር ክልል ተፈናቅለው በደሴና ኮምቦልቻ የሚገኙ ዜጎች ቁጥር ከ350 ሽህ በላይ ደርሷል፡፡
ከእነዚህ ተፈናቃዮች ውስጥ 12 ሺህ 352ቱ በኮምቦልቻና በደሴ ከተሞች በመጠለያ ውስጥ እንደሚገኙ የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መሳይ ማሩ ገልጸዋል፡፡
ለተፈናቃዮቹ ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም ከቁጥሩ አንጻር ማዳረስ እንዳልተቻለ የገለጹት ኀላፊው፥ የመረጃ ጥራት ችግር፣ የአቅርቦት መጓተት፣ የመድኃኒት እና አቅርቦት ችግሮች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይም በአዲስ መልክ ወደ መጠለያ የገቡትን እርዳታ ማዳረስ እንዳልተቻለ ገልጸው፥ አሁን ችግሩን ለመቅረፍ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ ፥ተፈናቃዮቹ ያሉበት ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡የሚሠራ እጅ እያላቸው እንዲህ ሲሆኑ መመልከት በጣም ልብ ይሰብራል ነው ያሉት፡፡
ምክትል አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ይህንን ሕዝብ መታደግና ወደነበረበት መመለስ ትልቅ ሥራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ችግሩ ከባድ እንደሆነ የገለጹት ምክትል አፈ ጉባኤዋ የደሴና የአካባቢዋ ማኅበረሰብ ላደረገው ትብብር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
“ረሃብ ጊዜ ዓይሰጥም፤ ሕጻን ለእናቱ ምግብ ሲላት የምትመልሰው ማጣትን የመሰለ ችግር ስለሌለ ኢትዮጵያውያን ቁርሳችንን ትተን ለእነዚህ ወገኖች እንድረስላቸው” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ችግሩን ተመልክቶ መፍትሔ ለመፈለግ መምጣታቸውን የተናገሩት የኢፌዴሪ የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው የተመለከቱት ችግር እንዲፈታ እንደ እናትም እንደ ሴትም ኢትዮጵያውያንን አስተባብረን እንመለሳለን ማለታቸውን አሚኮ ዘግቧል።
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
0
People Reached
0
Engagements
Boost Post
Like

Comment
Share
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.