Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ልዩነታቸውን በውይይት እንዲፈቱ ቻይና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አስታወቀች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከቻይና ስቴት ካውንስልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ ጋር የስልክ ውይይት አድርገዋል።

ሚኒስትሮች በነበራቸው የስልክ ውይይት በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ ሁለቱ ሃገራት ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

አቶ ገዱ የቻይና መንግስት ”በቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ” አማካኝነት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት የሚያስችል የቻይና አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤን እና የሚኒስትሮችን የቪዲዮ ኮንፍረንስ በቅርቡ በተሳካ ሁኔታ ማካሄድ በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

የኮቪድ ወረርሽኝን ለመግታት ቻይና ለኢትዮጵያ እያደረገች ላለው ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት ከቻይና ጋር የጀመረችውን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥልም አውስተዋል።

በተጨማሪም ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ሲሪል ራማፎሳ ሰብሳቢነት የተካሄደውን አስቸኳይ የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ቢሮ የቪዲዮ ስብሰባና ውሳኔ በተመለከተም ገለጻ አድርገዋል።

መሪዎቹ የናይልና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ የአፍሪካ ጉዳይ በመሆኑ ከአፍሪካ የሚመነጭ መፍትሄ እንደሚያስፈልገው መስማማታቸውን፤ በዚሁ መሰረት በግድቡ ሙሌት እና አስተዳደር ላይ የሚደረገው ድርድር በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት እንደሚጠናቀቅ መስማማታቸውንም አስረድተዋል።

በተጨማሪም የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩን መመልከት መጀመሩን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንዲገልጥ መወሰኑን በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በመሆኑም ጉዳዩ በአፍሪካ ህብረት በኩል መታየት በጀመረበት አግባብ እንዲፈታ ቻይና ድጋፏን እንድታደርግም ጠይቀዋል።

የቻይናው ስቴት ካውንስልና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በበኩላቸው ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ግንኙነት ልዩ ትኩረት ትሰጣለች ብለዋል።

ያላትን ትብብርም ይበልጥ አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅሰው ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ልዩነት በውይይት እንዲፈቱ ቻይና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.