Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ የሶስትዮሽ ድርድር ላይ የበኩሏን የግድብ ሙሌት ደንብ አቀረበች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 28፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሶስቱ ሀገራት መካከል እየተደረገ ባለው ድርድር ላይ የበኩሏን የግድብ ሙሌት ደንብ አቀረበች።

የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብፅ የውሃ ሚኒስትሮች የተሳተፉበት የሶስትዮሽ ድርድሩ በቪዲዮ ኮንፍረንስ በመታገዝ በትናንትናው እለት መካሄድ መጀመሩንም ይታወቃል።

የኢፌዴሪ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ፥ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የውሃ ሚኒስትሮች በትናንትናው እለት በሰጡት መመሪያ መሰረት የኢትዮጵያ፣ የሱዳን እና የግብፅ የህግ እና የቴክኒክ ቡድኖች የድርድር ስብሰባቸውን በዛሬው እለት ቀጥለው ማካሄዳቸውን አስታውቋል።

በድርድሩ ላይም የደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የአሜሪካ ታዛቢዎች እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት የመደባቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።

የዛሬው የድርድር ስብሰባ ሶስቱ ሀገራት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደንቦችን አስመልክቶ ስምምነት ባልተደረሱባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ ያለመ እንደነበረም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።

በዛሬው እለትም የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ቢሮ ሐምሌ 17 2012 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ መሰረት እንዲሁም የሶስቱ ሀገራት የውሃ ጉዳይ ሚኒስትሮች በትናትናው እለት በደረጉት ስብሰባ በጋራ ሰነድ ላይ ለመስራት ተስማምተዋል።

በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ የበኩሏን የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ደንብ ማቅረቧንም ነው ሚኒስቴሩ በመግለጫው ያስታወቀው።

ሱዳን እና ግብፅ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ደንብ ለመመልከት ጊዜ እንደሚፈልጉ ጠቅሰው፤ ስብሰባው እንዲራዘም ጠይቀዋል።

በዚህም መሰረት ሀገራቱ የውስጥ ምክክራቸውን ሲያጠናቅቁ ድርድሩን ለመቀጠል ከስምምነት መደረሱንም ነው ሚኒስቴሩ ያመላከተው።

የድርድር ስብሰባውም የግብፅ ልኡክ ባቀረበው ሀሳብ መሰረት ነሐሴ 4 2012 ዓ እንደሚቀጥልም ነው የሚጠበቀው።

ድርድሩ ከዚህ ቀደምም በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለ11 ቀናት ሲካሄድ ቆይቶ ባሳለፍነው ሐምሌ 6 2012 ዓ.ም መቋረጡ ይታወሳል።

ድርድሩ ተቋርጦ የቆየውም በሱዳን በኩል በቀረበው የይዘግይልኝ ጥያቄ መሠረት ሲሆን፥ ከትናንት ከሰዓት ጀምሮ መካሄድ ጀምሮ ነበር።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.