Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በታላቁ ሩጫ ላይ ናት! እንኳን ለ21ኛው የታላቁ ሩጫ ዝግጅት አደረሳችሁ- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ፣ ጥር 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 21ኛውን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ዝግጅት ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኢትዮጵያ ድህነትንና ኋላ ቀርነትን፣ ግጭትንና ጦርነትን፣ መለያየትንና መከፋፈልን ከኋላዋ ጥላ፤ ብልጽግናንና ሥልጣኔን፣ ሰላምንና መቻቻልን፣ አንድነትንና መግባባትን ለማስፈን ወደፊት እየሮጠች ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በታላቁ ሩጫ ላይ ስለሆነች፥ ታላቁ ሩጫ ለእኛ ከጤና፣ ከመዝናኛና ከኢኮኖሚ ጥቅሞቹ በላይ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ሩጫ አሸናፊ ሆኖ ብቻ እንዲጠናቀቅ ሳይሆን ኢትዮጵያችን ሪከርድ እንድትሰብር ጭምር እንፈልጋለን ነው ያሉት።
የምንወዳደረው ከብዙ ሯጮች ጋር መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ የምንፎካከረውም ከድህነት፣ ከጎጠኝነት፣ ከብልሹ አሠራር ከዋልታ ረገጥነት፣ ከውጭና ከውስጥ አፍራሾች ጋር ነው ብለዋል።
ያለ ምንም ጥርጥር ግን ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፤ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ሪከርድን ማንም እንዳይደረስበት አድርጋ ትሰብረዋለች ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ታላቅ ሩጫ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች፣ ከዚያም በመላዋ አፍሪካ፤ ብሎም በመላው ዓለም የኢትዮጵያን ስም የሚያስጠራ ታላቅ ክንዋኔ ሆኖ እንደሚስፋፋ እምነታቸው መሆኑን ገልጸው፥ ለዚህም መንግሥት አስፈላጊን ድጋፍ ሁሉ እንደሚሰጥ አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

 

ታላቁ ሩጫ ለእኛ ከጤና፣ ከመዝናኛና ከኢኮኖሚ ጥቅሞቹ በላይ ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በታላቁ ሩጫ ላይ ስለሆነች። ድህነትንና ኋላ ቀርነትን፣ ግጭትንና ጦርነትን፣ መለያየትንና መከፋፈልን ከኋላዋ ጥላ፤ ብልጽግናንና ሥልጣኔን፣ ሰላምንና መቻቻልን፣ አንድነትንና መግባባትን ለማስፈን ኢትዮጵያ ወደፊት እየሮጠች ነው።
አንድ የስፖርት ሰው ማሸነፍ ከፈለገ አምስት ነገሮች ያስፈልጉታል። የአካል ብቃት፣ በቂ ዝግጅት፣ ትጥቅ፣ ዲሲፕሊንና በመወዳደሪያው ላይ በጊዜውና በቦታው መገኘት። ኢትዮጵያም መደመር በሚባለው ጎዳና ብልጽግና የተባለውን ሜዳልያ ለማግኘት እየሮጠች ነው። በዚህ ሩጫ እንድታሸንፍ በሁለም መስኮች የመወዳደር ብቃት እንዲኖራት ማድረግ አለብን። ኢትዮጵያውያን በቂ የአካል፣ የመንፈስና የአስተሳሰብ ዝግጅት ያስፈልገናል። ለድሉ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ትጥቅ ወሳኝ ነው፤ ራሳችንን ከብዙ አጥፊ ነገሮች የሚጠብቅ ሀገራዊ ዲሲፕሊን ያስፈልጋል። የምንወዳደረው ከዓለም ጋር ስለሆነ በተገቢው መድረክ፣ ጊዜው ሳያልፍብን ተወዳዳሪ ሆነን መገኘትም አለብን። ዛሬ በዚህ ታላቅ ሩጫ ላይ የምትሳተፉ ሁሉ እያንዳንዱን ምእራፍ ስትሮጡ እየሮጠች ያለችውን ኢትዮጵያን እንድታስቧት አደራ እላለሁ።
የኢትዮጵያ ሩጫ አሸናፊ ሆኖ ብቻ እንዲጠናቀቅ አንፈልግም። ኢትዮጵያችን ሪከርድ እንድትሰብር ጭምር እንፈልጋለን። የምንወዳደረው ከብዙ ሯጮች ጋር ነው። ከድህነት ጋር እንፎካከራለን፤ ከጎጠኝነት ጋር እንፎካከራለን፤ ከብልሹ አሠራር ጋር እንፎካከራለን፤ ከዋልታ ረገጥነት ጋር እንፎካከራለን፤ ከውጭና ከውስጥ አፍራሾች ጋር እንፎካከራለን፤ ያለ ምንም ጥርጥር ግን ኢትዮጵያ ታሸንፋለች፤ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን ሪከርድን ማንም እንዳይደረስበት አድርጋ ትሰብረዋለች።
ታላቁ ሩጫ እንዲመሠረትና ታላቅነቱን እንዳከበረ እንዲቀጥል ያደረጉትን ሁሉ ላመሰግናቸው እወዳለሁ። በተለይም የሀገራችን ኩራት፤ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ፤ በመከራዋም ሆነ በደስታዋ ቀድመው ከሚደርሱላት አንዱ የሆነውን አትሌት ኃይሌ ገብረ ሥላሴን በዚሁ አጋጣሚ በራሴና በኢትዮጵያ ስም አመሰግነዋለሁ። ታላቅ ሰው ማለት ታላቅነቱን እንደጠበቀ፤ ለሀገሩ ታላቅ ሥራ የሚሠራ ማለት ነው። ሰው ያልፋል፤ ታሪክና ሥራ ግን ሲናገሩና ሲያስከብሩ ይኖራሉ። ኃይሌ በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያን በክብር አስጠርቷታል፤ ለብዙ ተተኪ አትሌቶች አርአያ ሆኗል። በተለያዩ ጥረቶች የሚገኝን ገንዘብ እንዴት ወደ ኢንቨስትመንት መቀየር እንደሚቻል ኃይሌ ምሳሌ ነው። ኃይሌ አትሌት ብቻ ሳይሆን መካሪ፣ አስታራቂ፣ ሽማግሌ ነው። ሀገሩ ስትደፈርም እንደ ነብር የሚቆጣ፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ቀልድ የማያውቅ መሆኑን በተደጋጋሚ አይተናል። ኢትዮጵያ እንደ ኃይሌ ያሉ ሚልዮኖችን ትፈልጋለች።
ባለፉት ሃያ ዓመታት ታላቁ ሩጫ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ማሰባሰብ ችሏል፤ በዓመት አንዴ ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለ አብሮነት ልባቸውን እንዲሰጡ አድርጓል። በሐይማኖታዊ በዓላት አብረው መሆን ያልቻሉ ዜጎች በታላቁ ሩጫ ተቃቅፈው ይሮጣሉ፤ በብሔረሰባዊ መሰባሰቦች አንድ ላይ መሆን ያልቻሉ ሕዝቦች ታላቁ ሩጫን ጠብቀው ይገናኛሉ። ኃይሌን በታላቁ ሩጫ ስናመሰግነው ዝግጅቱ ለአትሌቲክስ ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አኳያ ብቻ ሳይሆን፥ ኢትዮጵያዊ መሰባሰብን፣ ኢትዮጵያዊ ትስስርን፣ ኢትዮጵያዊ መቀራረብን የምንፈጥርበት፤ በብሔር፣ በቋንቋና በሐይማኖት የማንታጠርበት፣ የሁላችን የሆነ ታላቅ ዝግጅትን ስላስጀመረልን ጭምር ነው።
በዚህ አደባባይ በታላቁ ሩጫ ለመሳተፍ የመጣችሁት ሁሉ ኢትዮጵያን በልባችሁ ይዛችሁ እንደምታሸንፉ አምናለሁ። ብሔር፣ እምነት፣ የፖለቲካ አመለካከትና ጾታ ሳይለያችሁ አንድ ላይ ዛሬ እንደሮጣችሁት ሁሉ፤ ኢትዮጵያ በሁሉም ነገር አሸንፋ ሪከርድ እንድትሰብር አንድ ሆናችሁ በዓለም አደባባይ እንድትሮጡ አደራ እላለሁ። ይሄ ታላቅ ሩጫ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገሮች፣ ከዚያም በመላዋ አፍሪካ፤ ብሎም በመላው ዓለም የኢትዮጵያን ስም የሚያስጠራ ታላቅ ክንዋኔ ሆኖ እንደሚስፋፋ አምናለሁ። ለዚህም መንግሥት አስፈላጊን ድጋፍ ሁሉ ይሰጣል። ለኢትዮጵያ እንሩጥ፤ አንድ ሆነን ከሮጥን ኢትዮጵያ ታሸንፋለች።
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ጥር 15፣ 2014 ዓ.ም
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.