Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና አልጄሪያ በፋርማሲዩቲካልስ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአልጄሪያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ከአልጄሪያ የፋርማሲዩቲካልስ ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዶክተር ሎፍቲ ቤነብአህመድ በዘርፉ በትብብር ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

አምባሳደር ነብያት በሁለቱ ሀገራት መካከል በሁለትዮሽ ጠንካራ የፖለቲካ ግንኙነት እንዳለ ጠቅሰው በኢኮኖሚ ዘርፍ ግን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፋርማሲዩቲካልስ ዘርፍ አብዛኛውን የመድኃኒት ፍላጎቷን የምታሟለው ከውጭ በሚገባ ምርት መሆኑን የገለጹት  አምባሳደሩ፣ በዘርፉ ያለውን ምርታማነት ለማሳደግ እና የውጭ ኩባንያዎች በዘርፉ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ የሚያስችል ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ተቀርጾ የፋርማሲ ኢንዱስትሪ መንደር በመቋቋም እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በአልጄሪያ በዘርፉ የተሰማሩ ተቋማት ጋር በትብብር በመስራት፣ በፋርማሲዩቲካልስ እና መድኃኒት ማምረቻ እቃዎች ላይ ሀገሪቱ ያላትን ከፍተኛ ልምድ ለኢትዮጵያ ተቋማት እንድታካፍል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ሚኒስትሩ በበኩላቸው አልጄሪያ ከአመታት በፊት የመድሃኒት ምርት አቅርቦት እጥረትን ከውጭ በማስመጣት የምትሸፍን መሆኑን ገለጸው፣ መንግስት ባለፉት አስርት አመታት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን የመድሃኒት ፍላጎቷን በሀገር ውስጥ ምርት እንደምታሟላም አንስተዋል፡፡

አያይዘውም ሀገራቸው በፋርማሲዩቲካልስ እና መድኃኒት ማምረቻ እቃዎች ዘርፍ ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ለማካፍል ዝግጁ መሆኗን ጠቁመዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ የአልጄሪያ ኩባንያዎችም በኢትዮጵያ በዘርፉ እንዲሰማሩ ለማድረግ በሚሲዮኑ በኩል የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደሚደገፉ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዩ ዙሪያም ለሚኒስትሩ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ አሁን ያለው ሁኔታ መንግስት የህግ የበላይነት ለማስከበር የሚያደርገው እንቅስቃሴ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህም በአሁኑ ወቅት ለመገባደድ በመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኝ እና አጥፊው የህውሓት ጁንታም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለህግ ይቀርባል ብለዋል፡፡

ሚኒስትሩም ማንኛውም ሀገር መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር የመጀመሪያ ተልዕኮው መሆኑን በማስታወስ፣ በኢትዮጵያም በመንግስት በኩል እየተደረገ የሚገኘው ዘመቻም በዚሁ እይታ እንደሚመለከቱት መግለፃቸውን በአልጄሪያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያወጣው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.