Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ በድንበር ደህንነትና ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ ጥር 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና የጅቡቲ ብሄራዊ ፖሊስ ኃይል በድንበር ደህንነት፣ ሽብርተኝነትን በጋራ ለመከላከል፣ በአቅም ግንባታ እና በመረጃ ልውውጥ አብሮ ለመስራት ለፈረሙት ሰነድ ተግባራዊነት ቁርጠኛ መሆናቸውን ገለጹ፡፡
 
የፖሊስ መኮንኖችን በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርስቲ እና በጅቡቲ ፖሊስ አካዳሚ ለማሰልጠንና በመደበኛ የማማከር አገልግሎት እንዲሁም በመረጃ ልውውጥ አብሮ ለመስራት የስምምነት ሰነድ መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡
 
ተቋማቱ ለተፈረመው ሰነድ ተግባራዊነት ቁርጠኛ መሆናቸውን በዛሬው ዕለት በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ አረጋግጠዋል፡
 
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ለሁለቱ ሀገራት የፖሊስ ተቋሟት ትብብር መሰረትና መተላለፊያ እንደመሆኑ ታሪካዊ እንደሚሆን አንስተዋል፡፡
 
ከመግባቢያ ሰነዱ መፈረም በኋላ ሁለቱ የፖሊስ ተቋማት መረጃን እና ተፈላጊ ወንጀለኞችን በመለዋወጥ፣ የኢትዮ ጅቡቲ የገቢና ወጪ ትራንስፖርት መተላለፊያዎችን ደህንነት በመጠበቅ እና የፖሊስ መኮንኖቻችንን አቅም በመገንባት ብዙ እርምጃዎችን ተጉዘናል ብለዋል፡፡
 
ህወሓት እና መሰል የሽብር ቡድኖች የሚፈጥሩት የደህንነት ስጋት በአንድ ሀገር ላይ ተወስኖ የሚቀር ሳይሆን በአህጉራችን አፍሪካ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ላይ ተፅእኖ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡
 
የሽብር ቡድኖች ከምንም ጊዜውም በላቀ ሁኔታ በመቀናጀት አካባቢያችን እንዳይረጋጋ የሚያደርጉት እንቅስቃሴና የተደራጁ ድንበር ዘለል ወንጀሎች ትኩረታችንን የሚሹ ጉዳዮች ናቸው ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ እንደ ፖሊስ ተቋም ከምንጊዜውም በላይ ህብረታችንን የምናጠናክርበት ወሳኝ ጊዜ ነው ብለዋል፡፡
 
የጅቡቲ ብሄራዊ ፖሊስ ኃይል ዳይሬክተር ኮሎኔል አብዱላሂ አብዲ ፋራህ በበኩላቸው፥ የሁለቱም ሀገራት ፖሊስ ተቋማት ፍላጎታቸው አንድና ሰላምን ማረጋገጥ መሆኑን ጠቁመው፥ የጀመርነውን መልካም ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የተፈራረምነውን የመግባቢያ ሰነድ ወደ ፈፃሚ አካላት በማውረድ ለተግባራዊነቱ እንተጋለን ብለዋል፡፡
 
በፌዴራል ደረጃ የነበረንን የተጠናከረ ግንኙነት በተለይ ከሀገራችን ጋር ከሚዋሰኑት ከክልል ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጋር ተመሳሳይ ግንኙነት እንዲፈጠር ተጠናክረን እንሰራለን ነው ያሉት፡፡
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.