Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ጋር 800 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ የኃይል ግዢ ስምምነት ተፈራረመች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2012  (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ ከቱሉ ሞዬ ጂኦተርማል ጋር 800 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ የኃይል ግዢ ስምምነት በዛሬው እለት ተፈራረመች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እንዳስታወቁት፥ በዚህ ደረጃ በመንግሥትና በግል መካከል አጋርነት ሲመሠረት በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ስምምነቱ ኢትዮጵያ የጂኦተርማል ኢንዱስትሪ የማስፋፋት ጥረትን እና ቀጣይ የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያግዝ ኃይልን ያቀርባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፥ “የኢነርጂ ዋስትናችንንም ያረጋግጥልናል” ብለዋል።

ስምምነቱ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና የፈረንሳዩ ሜሪዲዬም ኢንቨስትመንት ኩባንያ መካከል የከርሰ ምድር
እንፋሎት ኃይል ማመንጫ ገንብቶ ኃይል ለመሸጥ የሚያስችል ነው።

በስምምነቱ ላይም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፣ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ፣ በአፍሪካ የሜሪዲዬም ኢንቨስትመንት ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የቱሉሞዬ ፕሮጀክት ሊቀመንበር ሚስተር ማቲው ፒለር እና የኮርቤቲ ተወካይ ናቸው፡፡

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት እንደተናገሩት፥ በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አማራጮችን በማስፋት የግል አልሚዎችን ማሳተፍ ተጀምሯል፡፡

አሁን የተፈረመው ሥምምነትም ፕሮጀክቱን እውን ለማድረግ ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረሱን ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሸዴ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ የኤሌክትሪክ ኃይል ስብጥሩን በማመጣጠን የሀገሪቱን ኢነርጂ የማምረት አቅም እንደሚያሳድግ በመግለፅ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚን የፈጠረ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ከኩባንያው ጋር የነበረው ድርድር ተጠናቆ ሥምምነት ላይ መደረሱ እንዳስደሰታቸው ጠቅሰው፤ የግል አልሚዎች ተሳትፎ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሚያደርገው የሃይል አቅርቦትና ስብጥር የሚግዝ መሆኑን በመግለጽ ሌሎችም የግል አልሚዎች በዚህ ረገድ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የቱሉሞዬ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት 150 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሲሆን፥ ግንባታውም በሁለት ምዕራፎች ተከፍሎ እንደሚከናወን ተጠቁሟል፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታም 50 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ዕቅድ የተያዘ ሲሆን፥ ግንባታውም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2023 ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ወቅት ተገልጿል።

ሁለተኛውን ምዕራፍ ደግሞ 100 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ከአውሮፓውያኑ ከ2023 በኋላ ገንብቶ ለማጠናቀቅ መታሰቡን ለማወቅ ተችሏል።

የፕሮጀክቱን ግንባታ የሚያከናውነው ቱሉሞዬ ጂኦተርማል ኩባንያ ሲሆን ፥የቁፋሮውን ሥራ ደግሞ ኬንያ ጀነሬሽን የተባለ የኬንያ ሥራ ተቋራጭ ያከናውናል፤ ሚኪዳ የተባለ ሃገር በቀል ኩባንያም እንደሚሳተፍ ማወቅ ተችሏል።

የቱሉሞዬ እና የኮርቤቲ ከእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት አጠቃላይ የፋይናንስ ወጪ እያንዳንዳቸው 800 ሚሊየን ዶላር በድምሩ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር እንደሆነም ነው በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት የተጠቆመው።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.