Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ከጥጥ ምርት ከፍተኛ ገቢ እንድታገኝ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጥጥ አምራቾች ለሚያነሷቸውን ጥያቄዎች መልስ በመስጠትና በመደገፍ ኢትዮጵያ ከጥጥ ምርት ከፍተኛ ገቢ የምታገኝበትን አሠራር እንደሚያስቀምጥ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ የጥጥ ምርትን ለማሳደግና የዘርፉን ችግር ለመፍታት ያለመ ውይይት በጎንደር ከተማ እያካሄደ ነው።

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የእድገትና ተወዳዳሪነት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታረቀኝ ቡሉልታ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች በአምራቾችና በአቅራቢዎች በኩል የሚስተዋሉ መሆናቸውን ጠቁመው÷ የጥጥ ምርትን በዓለም አቀፍ ገበያ በማስተሳሰር አምራቹና አቅራቢው የሚጠቀምበትን አማራጮች ማመቻቸት ይገባል ብለዋል፡፡

ጥጥ አምራቾችም የላቀ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በጥራት ሊያመርቱ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አምራቾች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች በአግባቡ ምላሽ በመስጠትና በመደገፍ ከጥጥ ምርት ሀገሪቱ ከፍተኛ ገቢ የምታገኝበትን አሰራር እናስቀምጣለንም ነው ያሉት፡፡

የአምራች ኢንዱስትሪዎች ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ለማ የጨርቃ ጨርቅ ልማትን ለማሳደግ የጥጥ ምርት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው÷ ምርትን በመደበቅ የግብይት ስርዓቱ ላይ ጫና ለማሳደር የሚሞክሩ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ከግብፅ በመቀጠል በአፍሪካ ከፍተኛ የሆነ ጥጥ የማምረት አቅም እንዳላትና በዓመት በ92 ሺህ ሄክታር  እስከ 63 ሺህ ቶን የማምረት አቅም እንዳላት ተመላክቷል፡፡

በሀገሪቱ 20 በጨርቃጨርቅና መሰል ተግባራት የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎች ቢኖሩም በቂ የጥጥ ምርት እየቀረበላቸው አለመሆኑም ተገልጿል፡፡

በቂ የጥጥ ምርትን ለማቅረብ÷ የግብርና ግብዓት እጥረት፣ የግብይት ስርዓት አለመሻሻልእንዲሁም የፀጥታና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የዘርፉ ማነቆዎች መሆናቸውን ጥጥ አምራቾች ተናግረዋል፡፡

ችግሮቹን ለመፍታትና የሚፈለገውን ያህል የጥጥ ምርት ለማምረትም÷ በመንግስት በኩል ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራ ይገባልም ተብሏል።

በሙሉጌታ ደሴ

 

 

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.