Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የሎጅስቲክስ እና ትራንስፖርት አገልግሎት ስርዓትን የማዘመን ስራ እያከናወነች ነው – አቶ ደመቀ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 13 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ጠንካራ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር የሎጅስቲክስ እና ትራንስፖርት አገልግሎት ስርዓትን የማዘመን ስራ እያከናወነች መሆኑን ተናገሩ።

በዳቮስ የኢኮኖሚክ ፎረም ላይ የሎጅስቲክስ እና ትራንስፖርት አገልግሎት ስርዓት ዙሪያ ዓለም አቀፍ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ትስስር ለመፍጠር የሎጅስቲክስ እና ትራንስፖርት አገልግሎት ስርዓትን ለማዘመን በትኩረት እየሰራች ነው ብለዋል።

መንግሥት የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማጠናከር ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም አንስተዋል።

ከዚህ ውስጥ የሎጅስቲክስ እና ትራንስፖርት አገልግሎት ስርዓትን ለማዘመን በመንግስት የተወሰዱት እርምጃዎች የግሉን ዘርፍ የሚያበረታቱ መሆናቸውንም አንስተዋል።

አያይዘውም ከተለያዩ ክፍለ አህጉራት ጋር ጠንካራ እና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለመፍጠር ደረጀቸውን የጠበቁ መሰረተ ልማት እና አገልግሎቶች በሂደት ይመቻቻሉም ነው ያሉት።

በመድረኩ የተሳተፉ የተለያዩ ሃገራት የፖለቲካ እና የቢዝነስ መሪዎች ኢትዮጵያ የሎጅስቲክስ እና የትራንስፖርት ዘርፍ ለማዘመን የሄደችበትን ርቀት አድንቀዋል።

በቀጣይ ኢትዮጵያ በሎጅስቲክስ እና በትራንስፖርት ዘርፍ በሚፈጠር ጠንካራ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ ትስስር በቅርበት እንደሚሰሩ መግለጻቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

በተያያዘም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ የኢኮኖሚ ሚኒስትር ሱልጣን ቢን ሰይድ አል ማንሱሪ ጋር ተወያይተዋል።

ውይይቱ በሁለቱ ሃገራት መካከል የነበረውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር እና ትብብር በቀጣይ ተጨባጭ የሆነ ዕድገት ማምጣት ወደ ሚቻልበት አግባብ ማሳደግ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነበር።

የኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ የኢኮኖሚ ትብብር ከሃገራቱ ታሪካዊ ግንኙነት ባሻገር የሁለት አህጉር ቀጠናዊ ትስስር ማሳያ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ከተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ ጋር ያላትን የኢኮኖሚ ትስስር ቀጠናው በሚጠይቀው የንግድ መስተጋብር በተሻለ አግባብ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ተናግረዋል።

የተባበሩት ዓረብ ኢሚሬትስ የኢኮኖሚ ሚኒስትር ሱልጣን ቢን ሰይድ አል ማንሱሪ በበኩላቸው፥ በሃገራቱ መካከል እያደገ የመጣው የኢኮኖሚ ትስስር ተጠናክሮ እንዲቀጥል እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.