Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የዓረብ ሊግ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ግብፅን በመደገፍ ያወጣውን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ አደረገች

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኢትዮጵያ የዓረብ ሊግ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ግብፅን በመደገፍ ያወጣውን የውሳኔ ሀሳብ ውድቅ አደረገች።

የዓረብ ሊግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ባለፈው ረቡዕ ባካሄደው ስብሰባው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ የግብፅን አቋም በመደገፍ የውሳኔ ሀሳብ ማውጣቱ አይዘነጋም።

ይህን የውሳኔ ሀሳብም የሊጉ አባል የሆነችው ሱዳን የታቃወመችው ሲሆን፥ የውሳኔ ሀሳቡ የዓረቡን ዓለም ከኢትዮጵያ ጋር የሚያጋጭ እና ተቀባይነት የሌለው ነው በማለት በሀሳቡ ላይ ስሟ እንዳይሰፍር እስከመጠየቅ በመድረስ ተቃውማለች።

በጉዳዩ ላይ የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ፥ የዓረብ ሊግ ግድቡን በተመለከተ ግብፅ የምትይዘውን አቋም እደግፋለሁ በማለት ያሳለፈውን የውሳኔ ሀሳብ ሲደረጉ የነበሩ ድርድሮች የያዟቸውን ቁልፍ እውነታዎች ከግንዛቤ ሳያስገባ ለአባል ሀገሩ ጭፍን ድጋፍ የሰጠበት ነው ብሎታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው በዚህ የሊጉ ስብሰባ ላይ የውሳኔ ሀሳቡን በተመለከተ ሱዳን የያዘችውን አቋም አድንቋል።

ሱዳን የዓረብ ሊግ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ አቀነባብሮ ያወጣውን የውሳኔ ሀሳብ በመቃወም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የምክንያታዊ እና የፍትህ ድምፅ ሆናለች ብሏል በመግለጫው።

ለዚህ በመርህ ላይ ለተመሰረተው እና በቀጣይ ሁሉንም ወገን ተጠቃሚ ለሚያደርገው ስምምነት መደረስ ጠቃሚ የሆነውን የሱዳንን አቋም ኢትዮጵያ እንደምታደንቅም ነው ያመለከተው።

መግለጫው ኢትዮጵያ ከዓረብ ሊግ አባል ሃገራት እና ህዝቦች ጋር የቆየና የጋራ ዕሴቶችን መሰረት ያደረገ፣ ማህበራዊና ባህላዊ ትስስሮሽ እንዳላትም አትቷል።

ዓረብ ሊግ የሁሉንም አካላት ፍላጎት ያማከለና እውነታን የተመረኮዘ አካሄድ ሊከተል እንደሚገባውም አንስቷል።

ከዚህ በተቃራኒው ሲሆን ግን የሊጉን ተዓማኒነት የሚያሳጣና፥ በዓለም አቀፍ መድረክ ሰላም፣ መረጋጋትና ትብብር እንዲኖር የሚያደርገውን ጥረት አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑም መግለጫው አስታውቋል።

ኢትዮጵያም የናይል ውሃን የተፋሰሱን ሃገራት በማይጎዳ መልኩ፥ የአሁኑን እና የወደፊቱን ትውልድ ፍላጎት ለማሟላት በሚያስችል አግባብ የመጠቀም መብት እንዳላትም ነው የገለፀው።

ከዚህ ባለፈም ወንዙ ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆኑ መጠን የጋራ ትብብርን በማይጎዳ መልኩ ፍትሃዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መርሆዎችን ትከተላለችም ነው ያለው።

መግለጫው አያይዞም ኢትዮጵያ በሚደረጉ ተደጋጋሚና ግልጽ ውይይቶች የሚያግባባ መፍትሄ ላይ ይደረሳል የሚል እምነት አላትም ብሏል።

ሊጉ በግድቡ ዙሪያ በኢትዮጵያ ላይ በዚህ መልኩ ጫና ለማሳደር እና የበላይነትን ለማሳየት መሞከሩ ገንቢ ያልሆነ እና አሁን ባለችው ዓለም ቦታ የሌለው መሆኑን አስታውቋል።

ኢትዮጵያ አሁንም በተደረሰው የመርህ ስምምነት መሰረት የጀመረችውን የውሃ ሙሌት እና ሀይል ማመንጨት ስራ እንደምታከናውንም አረጋግጧል።

ይህም የመርህ ስምምነት ኢትዮጵያ ከግድቡ ግንባታ ጎን ለጎን የውሃ ሙሌቱን እንድታከናውን የሚፈቅድ መሆኑንም ነው የገለፀው።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.