Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ የጎብኚዎች መዳረሻ ስፍራዎቿን በኦን ላይን ማስተዋወቅ ጀመረች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 10፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያን የጎብኚዎች መዳረሻ ስፍራዎች በኦን ላይን ማስተዋወቅ መጀመሩን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ የቱሪዝም ዘርፉ ኮሮና ወረርሽኝ ያሳደረበትን ተጽዕኖ የሚያገግምበትን አቅጣጫ በማስቀመጥ 3 በሊዮን ዶላር ለማግኘት ማቀዱን በሚኒስቴሩ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ተወካይ አቶ እንደገና ደሳለኝ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

በተጠናቀቀው በጀት አመት በኢትዮጵያ ኮሮና ባስከተለው ቀውስ ከዘርፉ ለማግኘት ከታቀደው ሁለት ሦስተኛውን ገቢ ብቻ ማሳካት መቻሉንም ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡

ባለፈው በጀት አመት ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ ተብለው ከተጠበቁ 1 ሚሊየን በላይ የውጭ ሃገር ጎብኚዎች ውስጥ 541 ሺህ ሰዎች ብቻ ጎብኝተዋል፡፡

ችግሩ የጉብኚዎችን ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ከመቀነሱ ምበተጨማሪ ቆይታቸውን አሳጥረው ወደ መጡበት እንዲመለሱ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡

ወደዚህ ለመምጣትም የሆቴል ምዝገባና መሰል ነገሮችን የጨረሱ ጎብኚዎች ባሉበት እንዲቆዩ ተገደዋልም ነው ያሉት፡፡

በበጀት ዓመቱም 2 ነጥብ 71 ቢሊየን ዶላር ከጎብኚዎች መገኘቱንም ተናግረዋል፡፡

በሃገር ውስጥ በቱሪዝም ዘርፉ የሚተዳደሩ ተቋማትንና ሰዎችን ለመደገፍ መንግስት 3 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወለድ አልባ ብድር መስጠቱንም ጠቅሰዋል፡፡

በያዝነው በጀት አመት ኢትዮጵያን ከሚጎበኙ 1 ነጥብ 5 ሚሊየን የውጭ ሃገር ጎብኚዎች ከ3 ቢሊየን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘት መታቀዱንም አስረድተዋል፡፡

ፎርብስ መጽሔት ከኮሮና በኋላ ሊጎበኙ ከሚገባቸው 10 ሃገራት መካከል ኢትዮጵያን በሰባተኝነት ማስቀመጡ ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.