Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተና አልፋ ሃያልነቷን ለዓለም እንደምታሳይ አልጠራጠርም-አቶ ጋዲ ይባርከን

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተና አልፋ ነገዋ የተሻለ እንዲሆን ማድረግ የሁላችንም ግዴታ ነው ሲሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊው የእስራኤል ፓርላማ አባል አቶ ጋዲ ይባርከን ተናገሩ።
የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስትሩ ዶክተር ሳሙኤል ኡርቃቶና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ሙሉ ነጋ ከእስራኤል ፓርላማ አባላትና ከሻሎም ኮፕስ የረድኤት ድርጅት የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
ውይይታቸው አገራቱ በሳይንስና በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ያላቸውን የቆየ ትብብር የበለጠ አጠናክረው በሚቀጥሉባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።
ትውልደ ኢትዮጵያዊው የእስራኤል ፓርላማ አባል አቶ ጋዲ ይባርከን በየትኛውም ቦታ የሚገኝ ኢትዮጵያዊ የተወለደባትና ያደገባት አገር ችግር ውስጥ ስትገባ ዝም ብሎ የማየት አቅም ሊኖረው አይገባም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከምትታወቅበት ድህነትና ችግር ወጥታ የተሻለ ደረጃ ላይ እንድትደርስ ማድረግ የእያንዳንዱ ሃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል።
“በእስራኤል የሚኖሩ ቤተ እስራኤላዊያን ከፖለቲካ ውጭ ቢሆኑም የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ደህንነት ግን ያሳስባቸዋል” ያሉት አቶ ጋዲ አገር ችግር ውስጥ ስትወድቀ ከጎኗ መቆምና የመፍትሄ አካል መሆን ግዴታ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ፈተና አልፋ ሃያልነቷን ለዓለም እንደምታሳይ “አልጠራጠርም” ያሉት አቶ ጋዲ ሁላችንም ከኢትዮጵያ መንግስት ጎን ለመቆም ዝግጁ ነን ብለዋል።
የሻሎም ኮፕስ ረድኤት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳንኤላ ብሌቸር በበኩላቸው አለምአቀፍ በጎ ፍቃደኞችን በመጠቀም የሁለቱን አገራት የረጅም ጊዜ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት የዓለምአቀፍ ትብብር ትስስርና አጋርነት ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ ደሳለኝ ሳሙኤል የአገራቱ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ከፓርላማ አባላቱ ጋር ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።
ይህም በኢትዮጵያ ያሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተሻለ ጥናትና ምርምር እንዲያደርጉ አቅም የሚፈጥርላቸው መሆኑን ተናግረዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.