Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 ዓ.ም የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 52 ነጥብ 1 ሚሊየን ለማሳደግ እንደሚሰራ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሃሴ 20፣ 2012(ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 ዓ.ም የደንበኞቹን ቁጥር ወደ 52 ነጥብ 1 ሚሊየን ለማሳደግ እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡

ተቋሙ የ3 አመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ እና የ2013 በጀት አመትን ዋና የቢዝነስ ትኩረት አቅጣጫን በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሪት ፍሬህይወት ታምሩ በሰጡት መግለጫ፤ የ3 አመቱ ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ ኢትዮ ቴሌኮም በተለዋዋጩ የዓለም ገበያ ውስጥ ተመራጭ የቴሌኮም ተቋም እንዲሆን የማድረግ አካል ነው ብለዋል፡፡

እስከ ፈረንጆቹ 2023 የሚቆየው ስትራቴጂካዊ ውጫዊውንም ሆነ ውስጣዊውን የገበያ ድርሻ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

ተፈጻሚ የሚሆን ዕቅድ ለማዘጋጀት ያግዛል ያሉት የ3 አመቱ ስትራቴጂክ እቅድ የባለድርሻ አካላትን ፍላጎት ይተነትናልም ነው ያሉት፡፡

ስትራቴጂው በደንበኞች እርካታና ተሞክሮ ማደግ ላይ ያተኩራል ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ ዕቅዱ ከተደራሽነት ባሻገር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የኩባንያውን ገፅታ ለማደስ እንደሚያስችልም ነው የጠቆሙት፡፡

ከዚህ አኳያም ባለፈው አመት የአራተኛ ትውልድ (4ጂ) ኔትዎርክን ማስጀመሩን በማስታወስ በቀጣይም የመሰረተ ልማት መስፋፋትንና የተጠቃሚውን ፍላጎት ከግምት ያስገባ የአምስተኛ ትውልድ (5ጂ) ኔትዎርክ አገልግሎትን ለማስጀመር ኩባንያው ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በ2013 በጀት አመት አጠቃላይ ገቢውን 55 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ለማድረስ ማቀዱንም ዋና ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል፡፡

ይህም በ2012 ከነበረው የ47 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር አመታዊ ገቢ የ16 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ያለው ነው፡፡

የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥርም ከነበረበት 44 ነጥብ 5 ወደ 48 ነጥብ 7 ሚሊየን ከፍ እንዲል እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡

የሶስተኛ እና አራተኛ ትውልድ ኔትዎርክ በተገቢው ባልተዳረሰባቸው የገጠር አካባቢ የሚገኙ ማስፋፊያዎች በ2013 በጀት አመት እንደሚጠናቀቁም ተገልጿል፡፡

ከዚህ ባለፈም በአዲስ አበባ የሚከፈቱ 150 ሳይቶችን ጨምሮ 842 አዳዲስ ማስፋፊያዎችን እንደሚተከሉም በዚህ ወቅት ተነስቷል፡፡

በሶዶ ለማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.