Fana: At a Speed of Life!

ኢጋድ ትናንት እና ዛሬ

ወቅቱ የአውሮፓውያኑ 1980ዎች መጨረሻ አካባቢ ነው ።ምስራቅ አፍሪካ በተለይ የአፍሪካ ቀንድ በተደጋጋሚ በድርቅ እና በጦርነት ከባድ ችግር ውስጥ የወደቀበት ነው።

የተለያዩ የአፍሪካ ቀጠናዎች በክፍለ አህጉር ደረጃ የሚያስተሳስራቸው የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር ጀምረዋል። የአፍሪካ ቀንድ ግን ወደዚህ ተግባር የገባው ዘግይቶ ነው። 1986 የምስራቅ አፍሪካ  የልማት እና የድርቅ መከላከል በይነ ድርጅት ሆኖ ጅቡቲ ዋና መቀመጫውን በማድረግ ተቋቋመ።

አሁን ላይ ስምንት አባል ሀገራት ያሉት  ድርጅት መጀመሪያ አላማው የአካባቢው ሀገራትን በተደጋጋሚ የሚያጠቃውን ድርቅ በጋራ መከላከል እና የጋራ ስትራቴጂ እየነደፉ ለልማት የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ አድርጎ መንቅሳቀስ ጀመረ።

ይህ ቀጠናዊ ድርጅት ከ10 ዓመት በኋላ በ1996 አላማውን እና ግቡን አስፍቶ ድጋሚ በአዲስ ማሻሻያ ተቋቋመ የአሁኑን ስምም ያዘ፤ድርቅ የሚለውን ቅጥያ አነሳ።

በማሻሻያው ውስጥም ለክፍለ አህጉሩ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም አካታች የልማት እንቅስቃሴዎች ላይ ትኩረቱን አደረገ።

በጉያው ከ267 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ይዟል፤ይህ የህዝብ ቁጥር ከአፍሪካ ጠቅላላ ህዝብ ብዛት 21 ነጥብ 5 በመቶ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገራት ጠቅላላ ህዝብ ደግሞ 26 ነጥብ 3 በመቶ ይዟል፤ ኢጋድ።

ቀጠናው በተደጋጋሚ ድርቅ የሚያጠቃው፣ ተለዋዋጭ የዝናብ መጠን ያለው፣ ግጭት የበዛበት ፣ደካማ ተቋማት ያሉበት፣ ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር የሚታይበት፣ድህነት እና ዝቅተኛ የጤና አግልግሎትን የሚያስትናግድ በግብርና እና በቁም እንስሳት ሃብት ላይ ጥገኛ የሆነ ነው።

የትምህርት ተደራሽነትም እንደ ቀጠና ከታየ አነስተኛ የሆነ የተማረው ህዝብ ቁጥር ብዛትም እንዲሁ የውጪ ንግድ ምርቱ ዝቅተኛ ነው ።

ድርቅን ለአብነት ስንወስድ 2011 ላይ 16 ሚሊየን ዜጎች ለከፋ ጉዳት የተዳረጉበት ሲሆን፥ 2016 ሚሊየኖችን አደጋ ላይ ጥሎ አልፏል።

ጎልማሳው ኢጋድ

ኢጋድ በ1996 የአሁኑን ስሙን ሲይዝ  ካስቀመጣቸው ግቦች ዋናው ሰላም እና መረጋጋትን ማምጣት ነው። አሁን ላይ ይህ ድርጅት ከተመሰረተ 33 ዓመታትን አስቆጥሯል።

በእነዚህ ሶስት አስርት ዓመታት ከሰላም እና መረጋጋት ከልማት ማምጣት አኳያ ያመጣው ለውጥ ምን ያህል ነው?

ከሱዳን እስከ ደቡብ ሱዳን ከሶማሊያ እስከ ጀቡቲ እና ኤርትራ ድረስ ብዙ ጉዳዮችን ለማሸማገል ጥሯል።

የደቡብ ሱዳን አሁንም መቋጫ አላገኘም  የሶማሊያ አካሄድ አሸባሪው አልሸባብ ሙሉ በሙሉ ባይከስምም ፤ ሞቃዲሾ ከመንግስት አልባነት በአንጻራዊ የተሻለ መንግስት አቋቁማ እየተጓዝች ነው ።

የተወሰኑ ምሁራን ኢጋድን በልፍስፍስነት ይተቹታል? የተወሰኑት ደግም ኢጋድ ባይኖር ኖሮ አሁናዊው የአፍሪካ ቀንድ ሁነት ሌላ ገጽታ ይኖረው ነበር ይላሉ።

አሁን ኢጋድ ልክ ራሱን እንዳደሰበት 1996 አዲስ ዋዜማ ላይ ነው ።

ማሻሻያዎችን ለማፅደቅ አዲስ አበባ ላይ ትናንት 47ኛውን የሚኒስትሮች መደበኛ ስብስባ አካሂዷል ቀጥሎም  የመሪዎች መደበኛ  ጉባኤ  በአዲስ አበባ አካሂዷል።

አምባሳደር ኢንጅነር ማህቡብ ማሌም ኢጋድን ለ11 ዓመታት በዋና ፀሃፊነት መርተውታል ፤ኢትዮዽያም በሊቀመንበርነት እንዲሁ ኢጋድን ለበርካታ ዓመታት መርታለች አሁን ኢንጂነሩ፣  በኢትዮጵያዊው የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር  ወርቅነህ ገበየሁ ተተክተዋል።

የኢጋድ ጅማሮ ተመሳሳይ የአኗኗር ዘይቤ እና የምጣኔ ሀብት መሰረት ያላቸውን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሀገራትን ብልፅግና ለማምጣት ታሳቢ ያደረገ ድርጅት  ሆኖ ነው ብቅ ያለው ።

ከቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ማግስት የበርካታ ዜጎች ህይወት የቀጠፈ ግጭት እና ጦርነት የተስተናገደበት የአለማችን አደገኛው ቀጠና ነው የአፍሪካ ቀንድ።

ከሰው ሰራሽ ግጭት እና ጦርነት የፖለቲካ ዥዋዥዌ የስልጣን ሽኩቻ የገፋቸው የእርስ በእርስ ጦርነቶች ምስራቅ አፍሪካን የግጭት ቀጠና የሚል ተቀጥያ አሰጥቶታል። በእርግጥ ስያሜው የአካባቢውን ምግባር የሚገልጥ ነው ።

የአፍሪካ ቀንድ ከሱዳን እስከ ሶማሊያ ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት እስከ አሁኑ የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ቀውስ፣ የአሸባሪው አልሸባብ እንቅስቃሴ ፣ሄድ  መለስ የሚለው የሶማሊያ የባህር ላይ ወንበዴዎች እንቅስቃሴ  በዚሁ የአፍሪካ ክፍል ነው።

የአፍሪካን ቀንድ በተደጋጋሚ የሚያጠቃው ድርቅ በተለይ  በኢጋድ አባል ሀገራት የአርብቶ አደር ማህብረሰቡን በከፍተኛ ደረጃ አደጋ ላይ ሲጥለው ተስተውሏል።

በዚህም የተነሳ የጋራ የድርጊት መርሃ ግብር በመቅረፅ ቅድመ መከላከል እና ማስጠንቀቂያ  እየሰጠ በመጓዝ ላይ ነው።ከአለም አቀፉ ማህበረሰብም ድጋፍ እና እርዳታ ለተጎጂዎች እንዲደርስ በዲፕሎማሲው አለም አፍ ሆኖ ይሰራል።

ኢጋድ በአካባቢው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን በርካታ የአሸማጋይነት ሚና ዎችን ተጫውቷል።በተቃራኒው ከኢትዮ- ኤርትራ  ጦርነት ማግስት ኤርትራ ከኢጋድ መውጣቷ የራሱን ተፅእኖ አሳርፎ ቆይቷል።

የአባል ሀገራቱ አልፎ አልፎ የሚታይ የጥርጣሬ ፖለቲካ እና  ለእጅ አዙር ጦርነቶች እና ግጭቶች መነሻ ሰበብ መፍጠር፤የድንበር ላይ ግጭቶች እና የደሴቶች እና የውሃማ አካባቢዎች የይገባኛል ጥያቄዎች እና እርኩቻዎች ለኢጋድ ፈተና እንደሆኑ ቀጥለዋል።

    ኢጋድ በተችዎቹ አይን

ኢጋድ በዲፕሎማሲ አጥኝ ተቺዎቹ ፊት ደካማ ድርጅት ሆኖ ይነሳል ።ድርጅቱ እስካሁን እንደ እድሜው የጎላ ሚና አልተወጣም እንዳውም እየተዳከመ መጥቷል በማለት ያነሳሉ ።

እንደ መከራከሪያ የሚያነሱት የቅርብ ሁነቱን የደቡብ ሱዳንን የአሸማጋይንቱን ጉዳይ ነው ፣ለጁባ ፖለቲካ አጭር እና ግልፅ የመፍትሄ ሀሳብ አላቀረበም ያ ባለመሆኑም እስከዛሬ ችግሩ እየተንከባለለ ነው ይላሉ።

ልማት በሚለው ላይም የተወሰነ ደረጃ መጓዝ ቢችልም በተለይ እንደ ሌሎች ተመሳሳይ ክፍለ አህጉራዊ ድርጅቶች ጎልቶ አልውጣም ።ኢኮዋስን(ECOWAS) በማሳያነት ያቀርባሉ ።

የአባል ሀገራቱ የተሰሚነት ካባ ድረባ እና ነጠቃ የሚደረግ  ከመጋረጃው በስተጀርባ  ያለው ሽኩቻም ለኢጋድ ረዥም ርቀት ያለመጓዝ እንደ ምክንያት ይንሳል።

ጠንካራ ተቺዎች ደግሞ የድርጅቱን የፋይናስ አቅም ያነሳሉ። የማሸማገልና የማደራደር ሃላፊነቱን በራሱ ገንዘብ አይወጣም በበጀት እጥረትም ሲፈተን ይስትዋላል ፤ያለ ፋይናንስ ነፃነት  የውሳኔ ነፃነት አይታሰብም በማለት ይሞግታሉ ።

እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለቀይ ባህር እና ለኤደን ባህር ሰላጤ ልዩ ትኩረት ሳይሰጥ በውስጥ ጉዳዩ ላይ ብቻ ማተኮሩም ፤ቀጠናው በሀያላን ሽኩቻ በአዳዲስ ሃይላት እንዲታመስ አድርጎታል በማለትም ይወቅሱታል ።

የኢትዮዽያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ግን ከኢጋድ ድክመቶች ይልቅ ጥንካሬዎቹ እና ስኬቶቹ ጎልቶ ይታያቸዋል።

ከአሁን በፊት አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው  47ኛው የኢጋድ የሚኒስትሮች መደበኛ ጉባኤ ላይ ባሰሙት ንግግር፥ ያለ ኢጋድ ተሳትፎ አሁናዊው የአካባቢው እንቅስቃሴ ማየት ከባድ ነበር ብለዋል።

ሚኒስትር ገዱ የኢጋድ ስኬቶች ብለው ካነሷቸው መካከል ጎልቶ የወጣው የሶማሊያ ጉዳይ ነው ።

ሶማሊያ ከአምባገነኑ ዚያ አድባሬ ውድቀት ማግስት መንግስት አልባ ሆና ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ነፍጥ ባነገቡ እና በጎሳ አለቃዎች ስትታመስ ከርማለች፣ በኢጋድ አሸማጋይነት እና አደራዳሪነት ረዳት አጋዥነት ግን የሶማሊያ ሁኔታ ተለውጧል።

በሶማሊያ ጉዳይ ከሶደሬ እስክ ባህርዳር  ከካይሮ እስክ አርታው በናይሮቢ ደግሞ በርካታ ጉባያት ተስተናግድዋል።

የሶማሊያ ጉዳይ ለበርካታ ዓመታት መፍትሄ አልባ ሆኖ የተጓዘው እንደ ኢትዮዽያዊው የምስራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ተንታኝ እና አንጋፋው ፀሃፊ የሱፍ ያሲን በብዕር ስማቸው ሀሰን ኡመር አብድላ፥ በሶማሊያ ጉዳይ የመድሃኒት ሰጪና የበሽታው ምንነት ገላጭ ሃኪሞች መበራከት እንጂ ማነስ አይደለም።

የመደራደርያ ሃሳቦች፣ የእርቅ አውርድ ጉባኤዎች አበዛዝና ጋጋታ ለጉድ ነው ይላሉ  ለቁጥር የሚያስቸግሩ የመፍትሄ ሀሳቦች መቅረባቸውን 1994 ዓመተ ምህረት ጦቢያ መፅጽሄት  ቅፅ 9 ቁጥር 10 ላይ ባሳተሙት የአፍሪካን ቀንድ በሚዳስሰው መጣጥፋቸው ።

ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገዱ አንዳርጋቸው  የዛሬይቱ ሶማሊያ ያለ ኢጋድ የአካባቢው ሀገራት ጎረቤቶቿ ድጋፍ ማለት ነው አሁናዊው ቁመናዋን ማሰብ ከባድ ነው ።

ኢጋድ በኢትዮዽያ ሊቀመንበርነት የሞቃዲሾ ምስቅልቅል  ገጽታ እንዲለወጥ ብዙ ደክሟል፤ አሁን ከሽግግር መንግስት ወደ አንድነት መንግስት መጥታ በየጊዜው ከራሷ ታሪክ ጋር ሲነጻጸር የተሻለ ምርጫ ከአንድም ሁለት ሶስቴ አድርጋለች ።

አሁናዊው ቁመናዋም በመንግስት ተቋማት ጥንካሬ ላይ ጥያቄዎች ቢነሱም፥ አሸባሪው አልሸባብ ሙሉ በሙሉ ባይከስምም የተሻለ ደረጃ ላይ ነች ።

ሚኒስትር ገዱ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የምጣኔ ሀብት ውህደት ለመፍጠር እያደረጉት ባለው እንቅስቃሴ በመሰረተ ልማት ትስስር ብዙ ርቀት መጓዛቸውን ተናግርዋል በእርግጥ ይህ ጉዳይ በገሃድ የሚታይ ነው።

ኢትዮዽያ- ከጅቡቲ፣ ኢትዮዽያ- ከሱዳን በመንገድ ተሳስራለች ከኬንያ ጋርም በፈጣን መንገድ ለመተሳሰር ግንባታው የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ይገኛል፤ የደቡብ ሱዳንም እንዲሁ በእነዚህ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ኢጋድ ጎልቶ ይውጣል ።

       ኢጋድ ከየት ወደየት ?

አምባሳደር ኢንጅነር ማህቡብ ማሌም ኢጋድን ለ11 ዓመታት በዋና ፀሃፊነት መርተውታል። የቀድሞው ዋና ፀሃፊ  ከኢጋድ ፈተናዎች አኳያ ሲናገሩ  ከውስጥም ከውጭም በርካታ መሰናክሎች ነበሩበት ይላሉ።

ውስጣዊው መሰናክል በሚል ካነሷቸው ነጥቦች መካከል የአባል ሀገራቱ አለመጠናከር፤ በድንበር ውዝግብ እና በተሰሚነት የፍላጎት ተቃርኖ መወጠር ናቸው።

ኢጋድ ለቀይ ባህር ፖለቲካ ትኩረት አልሰጠም፣ ኤድን ባህረ ሰላጤንም ዘንግቶት ቆይቷል፣ በውስጥ ጉዳዩ ላይ ብቻ በመስመጥ ይሉታል ድርጅቱን የገመገሙ የፖለቲካ ተንታኞች ።አምባሳደር ኢንጅነር ማህቡብ ግን ኢጋድ ትኩረት ነፍጎት አልቆየም ነው የሚሉት ።

እርሳቸው በቅርቡ የተቋቋመውን ኮሚቴ እና ለቀይ ባህር እና ኤደን ባህር ሰላጤን የሚከታተል ልዩ ልዑክ መሾሙን በማንሳት፣ቀይ ባህር እና የኤደን ባህር ሰላጤ አለማቀፋዊ ጉዳይ በመሆኑ በቀጣይም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ የቀድሞው  ዋና ፀሃፊ ተናግረዋል።

ኢጋድ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር ያለው  ግንኙነት ምን ይመስላል?

በእርግጥ ተመድ ኢጋድን እንደ ቁልፍ የሰላም እና ፀጥታ አጋሩ አድርጎ ይወስደዋልን ? አሁናዊው የሁለቱ ድርጅቶች ግንኙነት በምን መንገድ እየተጓዘ ነው ?

ፐርፌ ኦናንጋ አንያንጋ  የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ናቸው። ልዩ መልዕክተኛው ተመድ ከኢጋድ ጋር በርካታ ጉዳዮች ላይ በቅርበት እየሰራ ነው በሶማሊያ፣ በደቡብ ሱዳን በተለይ ሰፊ የትብብር ማዕቀፎች እንዳሉት ገልፀዋል።

የስዊዝ ቦይ ግንባታ ተጠናቆ ክፍት ከተደረገ በኋላ አለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ትኩረት ከሰጣቸው ስትራቴጂክ ቦታዎች መካከል ቀዳሚው የቀይ ባህር እና ኤደን ባህር ሰላጤ ጂኦ ፖለቲካ ጉዳይ ነው ።

በዚያ ያለውን ፍላጎት እና ጥቅም ለማስጠበቅ ሀገራት በጅቡቲ የጦር ሰፈራቸውን ገንብተዋል፤ ሃያላን ማለት ነው ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የቀይ ባህር ጂኦ ፖለቲካ በባህረ ሰላጤው የጋራ ምክር ቤት አባል ሀገራት የእርስ በእርስ ሽኩቻ ተፅዕኖው እያረፈበት ነው፤ የምስራቅ አፍሪካ የአፍሪካ ቀንድ ደግሞ የድምር ተዛማች ተጽዕኖ ዳፋ ገፈት ቀማሽ  እየሆነ ነው ።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዚህ ቀጠና ያለውን ሽኩቻ ለማስታገስ በየጊዜው በሚያደርገው ስብሰባ የውክልና ጦርነት ለመክፈት  የሚንቀሳቀሱ ሀገራትን እየገሰፀ ነው ብለዋል።

ልዩ መልዕክተኛው የተቋማት እና የድርጅቶች ጥንካሬ በአንድ ጀንበር የሚገነባ አይደለም ባይ ናቸው ።

እርሳቸው እንደሚናገሩት፥ በየጊዜው የሚደረጉ ማሻሻያዎች ድርጅትን ይገነባሉ ተመድም ሆነ ኢጋድ ከዚህ መስመር የሚያፈነግጡ አይደሉም።

ኢጋድ እና ኢትዮዽያ

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት እንዲመሰረት አዲስ አበባ ትልቅ ሚና ወስዳለች ።

ገና በማለዳው ያኔ ከደርግ ውድቀት ማግስት ኢትዮዽያ የተከተለቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቅድሚያ ለጎረቤት የሚል በመሆኑ፣ ከጎረቤቶቿ ጋር በቅርበት እና በእኩል ተጠቃሚነት ለመስራት ተንቀሳቅሳለች ።ኢጋድም የዚያ ውጥን አንድ አካል ነው።

ኢትዮዽያ ድርጅቱን እስከ  ቅርብ ወራት ድረስ  በሊቀመንበርነት ስትመራ ቆይታ ለሱዳን አስረክባለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብያት ጌታቸው አዲስ አበባ ከዲፕሎማሲ ስራዎች የመጀመርያው ረድፍ ላይ የሚገኝ በማለት ቀዳሚ  ትኩረት እንደተሰጠው  ተናግረዋል።ኢጋድ ዳግም ራሱን ካደሰ 23 ዓመታት አልፈዋል ተቺዎቹም ደጋፊዎቹም እኩል እየተናገሩ ዛሬ ላይ ደርሰዋል።

የዶክተር ወርቅነህ የቤት ሰራዎች ምን ሊሆኑ ይቻሉ ?

የጁባ የፖለቲካ ዥዋዥዌ፣ የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር እና የተቀናቃኛቸው የዶክተር ሪክ ማቻር የሽግግር መንግስት ምስረታ ሂደት የማራዘም ፖለቲካ የሄድ መለስ ስምምነት ትግብራ አሁንም ከቢሯቸው የሰነድ መደርደርያዎች ላይ ቀዳሚው ነው፡፡

ግጭት እና ሁከት የጥርጣሬ እና የእጅ አዙር ጦርነት ተጋላጭ የሆነው ቀጠና የዶክተሩን አመራር የሚፈትን ይሆናል ።

የቀይ ባህር እና የባህር ሰላጤው ጂኦ ፖለቲካም የዶክተር ወርቅነህ ገበየሁን ትኩረት የሚሻ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፤ በተለይ የባህረ ሰላጤውን ሀገራት የፍላጎት ተቃርኖ አስማምቶ የኢጋድ  አባል ሀገራትን ተጠቃሚነት የማረጋገጥ የቤት ስራ፡፡

አሁንም የኢጋድ የበጀት ክፍተት  እና የአባል ሀገራት የእርስ በእርስ የጥርጣሬ ዕይታ ለዶክተሩ ራስ ምታት ሊሆኑ ይችላሉ ።

 

 

በስላባት ማናየ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.