Fana: At a Speed of Life!

ኤክሳይዝ ታክስ ተጨምሯል የሚል የተሳሳተ ምክንያት አላስፈላጊ ዋጋ በሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ይወሰዳል

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 21፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ኤክሳይዝ ታክስ ተጨምሮብናል የሚል የተሳሳተ ምክንያት በማቅረብ በምርቶች ላይ አላስፈላጊ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው ገለፁ።

በአንዳንድ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ ተጨማሪ የኤክሳይዝ ታክስ ተጥሏል የሚል የተሳሳተ ህብረተሰቡን በማደናገር የዋጋ ጭማሪ ማድረግ የጀመሩ ነጋዴዎች መኖራቸውን በዛሬው ዕለት የኤክሳይዝ ታክስ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ ተገልጿል።

የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደገለፁት በነባሩ አዋጅ ላይ የኤክሳይዝ ታክሳቸው ከፍ ብለው የነበሩ በረቂቅ አዋጁ ማህበረሰቡ ጋር ሰፊ ጠቀሜታ ያላቸው እንዲቀነሱ ተደርጎ ሳለ በግንዘቤ ክፍተት በበርካታ ምርቶች ላይ ኤክሳይዝ ታክስ እንደተጨመረ ተደርጎ ለህብረተሰቡ ሲገለፅ ነበረ፤ ይህ ሁሉንም ስለሚጎዳ ይህንን የሚያደርጉ አካላት ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል ብለዋል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እሸቴ አስፋው በበኩላቸው፥ በአንዳንድ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎች እንዳሉ ጠቁመው፤ ነጋዴዎቹ ለሸማቹ የሚሰጡት ምክንያት የኤክሳይዝ ታክስ በመጨመሩ ነው የሚል የተሳሳተ ምክንያት እንደሚያቀርቡ ገልፀዋል።

ረቂቅ አዋጁ ላይ የታክስ መጣኔያቸው ዝቅ እንዲል የተደረጉ የፍጆታ ዕቃዎች ሳይቀር ዋጋ ለመጨመር የሚደረጉ ሙከራዎች ስላሉ ከዚህ አንፃር የመጀመሪያው ስራ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው አክለውም ድርጊቱ ህገ ወጥ በመሆኑ ሚኒስቴሩ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ተከታትሎ እርምጃ እንደሚወስድ መናገራቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.