Fana: At a Speed of Life!

ኤጀንሲው ከቻይና መንግስት የተገኙ የኮሮናቫይረስ መከላከያ የህክምና ግብዓቶችን ማሰራጨት ጀመረ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ በቻይና መንግስት በእርዳታ የተሰጠውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ የህክምና ግብዓቶችን ማሰራጨት መጀመሩን ገለፀ።

የህክምና ግብዓቶቹን ከትናንት መጋቢት 23 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለክልሎች እና ለከተማ አስተዳደሮች ማሰራጨት መጀመሩን በኤጀንሲው የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች የክምችትና ስርጭት ዳይሬተር አቶ እንዳልካቸው መኮነን ገልፀዋል።

እየተሰራጩ ያሉ የህክምና ግብዓቶች ቫይረሱን ለመለየት የሚረዱ የሙቀት መጠን መለኪያ፣ የፊት መሸፈኛ ጭምብል፣ የፊት መሸፈኛ ፕላስቲክ፣ የህክምና ባለሙያዎች የሚለብሷቸው መከላከያ ልብሶች መሆናቸውን አቶ እንዳልካቸው አስታውቀዋል።

እነዚህ ለኮቪድ – 19 ኮሮናቫይረስ ለመለየትና ለመከላከል የሚውሉ የህክምና ግብዓቶችን ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ላቋቋሟቸው የህክምና ለይቶ ማቆያ ተቋማት የሚሰራጭ መሆኑም ታውቋል።

የህክምና ግብዓቶቹ በኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በሰጠው የስርጭት ክፍፍል መሰረት እየተሰራጨ መሆኑን ዳይሬክተሩ መግለጫቸውን ከኤጀንሲው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.