Fana: At a Speed of Life!

እስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ ሕጻናት በኤድስ እንዳይያዙ ለማረጋገጥ የሚሰራ ዓለም አቀፍ ጥምረት ተመሰረተ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሕፃናት በኤድስ እንዳይያዙ የሚሰራ ዓለም አቀፍ ጥምረት መመስረቱን የዓለም ጤና ድርጅት በይፋዊ ገጹ አስታውቋል፡፡

ጥምረቱ እስከ ፈረንጆቹ 2030 ድረስ ማንኛውም ሕጻን ከኤድስ ነጻ እንዲሆን የማድረግ ግብ እንዳለው ተጠቁሟል።

እስካሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኤች አይ ቪ ጋር ከሚኖሩ ሕጻናት መካከል 52 በመቶዎቹ ብቻ ሕይወት-አድን ሕክምና እንደሚያገኙ  መረጃዎች ያመላክታሉ።

በሌላ በኩል 76 በመቶ ያህል ኤች አይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ አዋቂዎች የፀረ-ኤች አይቪ መድሃኒት እንደሚጠቀሙ የተመላከተ ሲሆን ይህም ከአዋቂዎች አንጻር ለሕፃናቱ በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠ የሚያመላክት ነው ተብሏል፡፡

ለችግሩ እልባት ለመስጠትም “ዩ ኤን ኤይድስ”፣ “ዩኒሴፍ” እና “የዓለም ጤና ድርጅት” አዲስ ጥምረት መስርተዋል።

ጥምረቱ የተመሰረተው ኤች አይቪ ቫይረስ በደሙ የሚገኝ ሕፃን ህክምና እንዲያገኝ ለማድረግ እንዲሁም አዲስ በኤች አይቪ የሚያዙ ሕፃናት እንዳይኖሩ ለመከላከል መሆኑ ተገልጿል።

ከተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች በተጨማሪ ጥምረቱ የሲቪል ማኅበረሰብ አካላትንም እንደሚያካትት ዘገባው አመላክቷል፡፡

ዓለም አቀፍ አጋሮችን፣ በተለይም ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድጋፍ ላይ የሚሰሩ ተቋማትን ጨምሮ በከፍተኛ ሁኔታ በኤች አይቪ ኤድስ የተጠቁ ዜጎች የሚገኙባቸው ሀገራት በጥምረቱ ተካተዋል ተብሏል፡፡

በመጀመሪያው ምዕራፍም 12 ሀገራት ጥምረቱን የተቀላቀሉ ሲሆን እነዚህም፡- አንጎላ፣ ካሜሩን፣ ኮትዲቯር፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ዑጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ እንደሆኑ ነው ዘገባው የዘረዘረው፡፡

ጥምረቱ በቀጣይ ለነፍሰ ጡር እና ለሚያጠቡ ልጃገረዶች እና ሴቶች ትኩረት በመስጠት፣ ከኤች አይቪ ጋር የሚኖሩትን የሕክምና ክፍተቶች መዝጋት እና የሕክምናውን ቀጣይነት ማመቻቸት ቀዳሚው መሆኑ ተጠቁሟል ፡፡

አዲስ የኤችአይቪ ተጋላጭነት እንዳይኖርም መከላከል ሌላኛው የትኩረት አቅጣጫ ነው፡፡

ተደራሽ የሆነ የኤች አይ ቪ ምርመራ፣ የተመቻቸ ሕክምና እና አጠቃላይ እንክብካቤ እና መብቶችን ማረጋገጥ ተጨማሪ የጥምረቱ ተልዕኮ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.