Fana: At a Speed of Life!

እነ እስክንድር ነጋን ጨምሮ 5 ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ህግ ምስክሮቼ ከመጋረጃ ጀርባ ይመስክሩልኝ ሲል ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ሆነ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እነ እስክንድር ነጋን ጨምሮ 5 ተከሳሾች ላይ ዐቃቤ ህግ ለምስክሮቼ ደህንነት ከመጋረጃ ጀርባ ይመስክሩልኝ ሲል ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ ሆነ።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የህገ መንግስት እና የፀረ ሽብር ጉዳዮች ወንጀል ችሎት የተከሳሾችን የክስ መቃወሚያ ተከትሎ ዐቃቤ ህግ ያቀረበውን ምላሽን ተመልክቶ ትዕዛዝ ለመስጠት ነበር ለዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠው።
ዐቃቤ ህግ ከዚህ በፊት በነበረው ቀጠሮ የማሰማቸው ምስክሮቼ ለደህንነታቸው ሲባል በምስክር ጥበቃ አዋጅ መሰረት ከመጋረጃ ጀርባ እንዲመሰክሩልኝ ሲል ማመልከቱን ተከትሎ ተከሳሾች ከመጋረጃ ጀርባ መባሉ ተገቢነት የለውም ሲሉ መቃወሚያ ማሰማታቸው ይታወሳል፡፡
ምስክሩ መስማትና ማየት እንደሚችል ማረጋገጥ ካልቻሉ የመስቀለኛ ጥያቄ ለማቅረብ አያስችልም፤ ምስክሩ ከመጋረጃ ጀርባ ሲመሰክር ተጨማሪ ሰነድ ይዞ እያነበበ ስለመሆኑ ምንም የምናውቀው ነገር አይኖርም ሲሉም ተቃውመው ተከራክረው ነበር።
በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ መዝገቡን መርምሮ ዐቃቤ ህግ ያቀረበው ምስክሮቼን ከመጋረጃ በስተጀርባ ላሰማ ጥያቄን ውድቅ አድርጓል።
በተያያዘ በችሎቱ ያልተገኙ 6ኛ እና 7ኛ ተከሳሾችን ከዚህ በፊት የፌደራል ፖሊስ አፈላልጎ ለችሎት እንዲያቀርብ በታዘዘው መሰረት ፖሊስ አድራሻቸውን ማግኘት አልቻልኩም በማለቱ ፍርድ ቤቱ ክሳቸው እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ችሎቱ የተከሳሾቹን አድራሻ ማወቅ ባለመቻሉ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ክሳቸው እየተሰማ ያሉ ተከሳሾችን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብታቸውን የሚያጣብብ በመሆኑ ነው ክሳቸው እንዲቋረጥ ያዘዘው።
የተሻሻለውን ክስ ለመጠባበቅ ለታህሳስ 13 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በታሪክ አዱኛ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል www.youtube.com/fanatelevision ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.