Fana: At a Speed of Life!

እናት ባንክ የብድር ወለድ ስረዛና የአገልግሎት ማሻሻያ አደረገ

አዲስ አበባ፣ግንቦት6፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) እናት ባንክ ለተለያዩ የብድር ዘርፎች የብድር ወለድ ስረዛና የአገልግሎት ማሻሻያ ማድረጉን አስታወቀ።

ባንኩ በሰጠው መግለጫ ኮረና ቫይረስ  በወረርሽኝነት በአለምአቀፍ ደረጃ መሰራጨት ከጀመረበት ወቅት አንስቶ በአለም ማህበረሰብ ላይ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶችን በማድረስ ላይ  እንደሚገኝ ጠቅሷል።

ይህ አለም አቀፍ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ   የንግድ እንቅስቃሴና በንግዱ ማህበረሰብ ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት በማድረስ ላይ መሆኑን ነው የገለጸው፡፡

በመሆኑም ባንኩ ይህንን ጉዳይ በከፋተኛ ሁኔታ ከግንዛቤ በማስገባት  በተለያዩ የስራ ዘርፎች ላይ ለተሰማሩ ተበዳሪዎቹ የብድር ወለድ ስረዛና የተለያዩ የአገልግሎት ማሻሻያዎችን  ማድረጉን ነው የተናገረው፡፡

የማሻሻያው ዋና ዓላማም እየተከሰተ ያለውን ችግር በጋራ ለመወጣት፣  በደንበኞች የንግድ እንቅሳቃሴ  ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመቀነስ፣ የብድር አመላለስን የተሻለ ለማድረግና የአገራችን  ኢኮኖሚ ሚዛናዊነቱን ጠብቆ ማስኬድ በሚቻልበት አካሄድ ባንኩ የራሱን ድርሻ ለመወጣት ታሳቢ ያደረገ  ነው ብሏል ።

በዚህም መሰረት የብድር ወለድና አገልግሎት ክፍያን አስመልክቶ በሆቴልና ቱሪዝም የስራ ዘርፍ ላይ ለተሰማሩ ደንበኞች ከግንቦት እስከ ሀምሌ የብድር ወለድ እንዳይከፍሉ መሰረዙን ገልጿል።

ከዚያም ባለፈ የብደር ማራዘሚያ ላይ የሚከፈለዉ የአገልግሎት ዋጋ ፣የኦቨር ድራፍት እድሳት ላይ የሚከፈለዉ የአገልግሎት ዋጋ ፣ብድራቸውን ከሚጠበቅባቸው የመክፈያ ጊዜ ቀድመው ለሚከፋሉ ደንበኞች ይጣል የነበረው ቅጣት እንዲሁም  ውዝፍ የብድር እዳን አዘግይቶ ሲከፈል የሚጣል ቅጣት ሙሉ ለሙሉ መነሳቱንም ነው ያብራራው።

በአለምአቀፍ ባንኪንግ ዙሪያም  ባንኩ የተለያዩ ማሻሻያዎች ማድረጉን ገልጾ በዚህም አስመጪዎች እቃ ወደ ሃገር ለማስገባት ለከፈቱት ሌተር ኦፍ ክሬዲት (LC) አሁን በአለም ላይ ከተፈጠረዉ ችግር አኳያ አስቀድመዉ  ለማራዘሚያ የሚጠየቁት የአገልግሎት ክፍያ ሙሉ ለሙሉ እንዲነሳ መደረጉን አንስቷል።

በተያያዘም  ከኮቪድ 19 ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን ዕቃዎች ለሚያሰመጡ  አስመጪዎች ባንኩ  ሃምሳ በመቶ (50%) የአገልግሎትና የኮሚሽን  ክፍያ መቀነሱን ነው የገለጸው፡፡

ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነትን ለመወጣትና ኮረና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ለብሄራዊ የኮቪድ 19 ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ  የብር 2 ሚሊዮን ብርድጋፍ ከማበርከቱም ባለፈ የባንኩ ሰራተኞችና የደንበኞች ደህንነት ከወረርሽኙ ለመጠበቅ  የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ መሆኑን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

 

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.