Fana: At a Speed of Life!

“እኔ እጄን በአግባቡ እታጠባለሁ ሕይወትም አድናለሁ!” በሚል መሪ ቃል ለአንድ ወር የሚቆይ እጅ የመታጠብ ንቅናቄ ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) “እኔ እጄን በአግባቡ እታጠባለሁ ሕይወትም አድናለሁ!” በሚል መሪ ቃል ከዛሬ ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ እጅ የመታጠብ ንቅናቄ በይፋ ተጀምሯል፡፡

በዓለም ለ13ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ12ኛ ጊዜ በሚከበረው የእጅ የመታጠብ ቀን ይፋ የተደረገው ንቅናቄ ለአንድ ወር እንደሚቆይ ነው የተነገረው፡፡

ንቅናቄው ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ሰው እጁን በአግባቡ በመታጠብ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ንቅናቄውን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ተናግረዋል፡፡

እጅን መታጠብ የሚያስገኘውን የጤና ጠቀሜታ በመረዳት ከእጅ ንጽህና ጉድለት የተነሳ ከሚመጡ በሽታዎች ራስን መከላከል ይገባልም ብለዋል፡፡

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት እጅን በአግባቡ መታጠብ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እና ለመከላከል የሚኖረውን ጠቀሜታ በመረዳት የዓለም ጤና ድርጅት በሚመክረው መንገድ ለሃያ ሰከንድ እጅን በሳሙና በአግባቡ መታጠብ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

የአይን ኢንፌክሽን፣ ከንጽህና ችግር የሚከሰቱ በሽታዎች እንዲሁም በጤና ተቋማት የሚከሰቱ የኢንፌክሽን ችግሮችን ለመቅረፍ የእጅ ንጽህናን ለመጠበቅ ተገቢው የውሃ አቅርቦት ስራ ሊሰራ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

በቅርቡ ትምህርት ሊከፈት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በትምህርት ቤቶች ያለውን የመታጠቢያ አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ተገቢው ስራ እየተሰራ መሆኑን ከጤና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.